FDRE Ministry of Agriculture

የተስተካከለ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም III

የተስተካከለ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም III ዋና ዓላማ የተሻሻለ የመሬት ይዞታ ዋስትናን በማረጋገጥ እና አነስተኛ አርሶአደሮችን በተለይም ሴቶችና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርናን እንዲተገብሩ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ ማስቻል ነው።

ከመስከረም 2017 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 2020 ዓ.ም የሚቆየው ይህ ፕሮግራም፣ የገጠሩን ህዝብ ፍላጎት የሚያሟላና የመሬት መረጃን በስፋት የሚጠቀም ቀጣይነት ያለው የመሬት አስተዳደር አገልግሎት ለመስጠት ታቅዷል። ለዚህም የፊንላንድ መንግስት 9.5 ሚሊዮን ዩሮ ሲመድብ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ የ1.5 ሚሊዮን ዩሮ በዓይነት የሚደረግ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

ፕሮግራሙ በዋናነት አዳዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ መስጠትን ከማጠናቀቅ ባለፈ ብሔራዊ የገጠር መሬት አስተዳደር መረጃ ሥርዓትን በማዘመን ከሌሎች ዘርፎች ጋር የማገናኘት ሰፊ ስራ ይሰራል።

በመሆኑም የአውሮፓ ህብረት የቡና ኤክስፖርት ደንቦችን ለማሟላት፣ ለአነስተኛ አርሶአደሮች የፋይናንስ አቅርቦትን ለማመቻቸት፣ የማዳበሪያ ስርጭትንና የገበሬዎችን መረጃ ለማቀናጀት እንዲሁም ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዘ የብድር ዋስትና ዘዴን ለማመቻቸት የሚረዳ ሲሆን በተጨማሪም ሥርዓቱ ከፋይዳ (FAYDA) ዲጂታል መታወቂያ እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተንቀሳቃሽ ንብረት ምዝገባ ሥርዓት ጋር እንዲገናኝ የሚያደርግ ፕሮግራም ነው።

በተጨማሪም ፕሮግራሙ ለእያንዳንዱ የመሬት ይዞታ የተለየ የአፈር ጤና እና የአየር ንብረት የሚቋቋም ግብርና ሰነዶችን በማዘጋጀት አርሶ አደሮችና የፋይናንስ ተቋማት መሬትን እንደ ዋስትና እንዲጠቀሙ የሚያስችል የሙከራ ስራዎችን ያከናውናል።

የተስተካከለ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም III ከአማካሪ ድርጅት ጋር በመቀናጀት በተመረጡ ክልሎች ከሚገኙ የመሬት ቢሮዎች ጋር በቅርበት ይሰራል። ፕሮግራሙ በሁሉም ክልሎች ላይ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በተለይም በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል።

ዋና ተጠቃሚዎቹ በመጀመሪያ ደረጃ ሴቶችና ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ አነስተኛ አምራች አርሶ አደሮች ሲሆኑ በተጨማሪም በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመሬት አስተዳደር አገልግሎት ሰጪዎች (የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ የመሬት አስተዳደር ኮሚቴዎችና ባለሙያዎች) ናቸው።

የተስተካከለ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም III “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” እና “የኢትዮጵያ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ኢንቨስትመንት ማዕቀፍ” ላሉ ሀገራዊ ራዕዮች ድጋፍ ይሰጣል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ተከታታይነት ያለው እና የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው።