FDRE Ministry of Agriculture

የተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም

የተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም/Participatory Agriculture and Climate Transformation Program (PACT) በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ The International Fund for Agricultural Development (IFAD) እና በሌሎች የልማት ድርጅቶች የሚደገፍ ሲሆን የትግበራ ጊዜውም እ.አ.አ ከየካቲት 2024 እስከ 2030 ድረስ የሰባት ዓመት ቆይታ ይኖረዋል። አጠቃላይ በጀቱም 193 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡

ግብርና እና የአየር ንብረትን አጣምሮ በግብርና ዘርፍ ዘላቂ እድገት ለማምጣት የሚሰራው ፕሮግራሙ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአየር ንብረት፣ በግብርናና አመጋገብ ስርዓት መሻሻል ላይ አቅዶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

የፕሮግራሙ ዓላማ በተመረጡ ቀበሌዎች ውስጥ 150,000 ቤተሰቦች (ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች) የገቢ፣ የምግብ እና የምግብ ዋስትናን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እንዲያሻሽሉ እና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶችን የመቋቋም አቅም እንዲገነቡ ማስቻል ነው።

በዚህም ሴቶችን፣ ወንዶችን፣ ወጣቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የአካቶ ትግበራ ስልትን ይተገብራል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የግብርና ግብዓቶች ለማቅረብ፣ የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል፣ የሴቶችንና የወጣቶችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት በትኩረት ይሰራል።

ሴቶችን በማብቃትና ኑሯቸውን ለማሻሻል በቁርጠኝነት የሚሰራ ፕሮግራም ሲሆን 50 በመቶ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል። በተጨማሪም በፕሮጀክቱ ስነ-ምህዳራዊ አውድ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ እና አቅም የሚገድቡ ችግሮች እንዲፈቱ ይሰራል።

ፕሮግራሙ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ እና በአፋር ክልሎች እየተተገበረ ሲሆን በዚህም 91 የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው ወረዳዎች እና በተለያዩ 151 ስነ-ምህዳሮች ላይ ይሰራል፡፡

በአጠቃላይ የፕሮግራሙ ቁልፍ ክፍሎች ሶስት ናቸው፡፡ እነሱም ማህበረሰብ መር፣ ለምርታማነት ተስማሚ የአየር ንብረትና ስነ-ምዕዳር እንዲሁም የግብርና ንግድ ልማት እና የተቋምና የፖሊሲ ማጠናከሪያና የመተግበር ድጋፍ አገልግሎት ናቸው፡፡