FDRE Ministry of Agriculture

የብዙ ሀገራት የስልጣኔ መሰረት የሆነው የጥጥ ሰብል!

ጥጥ በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን አሜሪካ እና እንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮትን ሲያቀጣጥሉ ከፍተኛ ድርሻን ያበረከተ ሰብል ሲሆን አሁን ለደረሱበት ዕድገት መሰረት እንደሆነም ይነገራል፡፡

ጥጥ ባለው ረዥም የእሴት ሰንሰለትና ቅብብሎሽ ምክንያት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የሚታወቅ ሲሆን አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ 250 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ በዓመት 1.5 ትሪሊየን የአሜሪካን ዶላር አመታዊ የጥጥ ንግድ ልውውጥ ይደረጋል፡፡ እንደዓለም አቀፍ የጥጥ አምራች ሃገራት ህብረት መረጃ መሰረትም በየዓመቱ ከ30 እስከ 34 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጥጥ ሰብል የሚሸፈን ሲሆን በዓለም ላይ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ቻይና እና ፓኪስታን ቀዳሚዎቹ ጥጥ አምራች ሀገራት በመሆን ተቀምጠዋል፡፡ በምርት ረገድም በየዓመቱ በአማካይ ከ26 እስከ 27 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ይመረታል፡፡

በአህጉራችን አፍሪካ ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቫር እና ማሊ ግንባር ቀደም ጥጥ አምራች ሀገራት ቢሆኑም እሴት በመጨመር ብዙም ያልገፉበት በመሆኑ የሚያመርቱትን ጥጥ ኤክስፖርት በማድረግ በቀጥታ የውጪ ምንዛሪ ግኝት ይጠቀሙበታል፡፡

በአንፃሩ ግብፅ እሴት በመጨር በየዓመቱ በአማካይ 550 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከጥጥና ከጥጥ ምርቶች ኤክስፖርት ገቢ ታገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ ከግብፅ በመቀጠል የሚያመርቱትን ጥጥ በሀገር ውስጥ እሴት በመጨመር የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ጥጥን በማምረት በርካታ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት ብትሆንም በሰፋፊ እና የተሻሻለ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥጥ ማምረት የተጀመረው በ1960ዎቹ ሚቼልኮት በተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ነበር፡፡

በወቅቱ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ የጥጥ ልማቱም እየተስፋፋ ሽፋኑ እስከ 140 ሺህ ሄክታር ደርሶ የነበረ ቢሆንም በ1974 ዓ.ም ኢትዮጵያ ወደ ሶሻሊዝም ስርዓት ባደረገችው ለውጥ ምክንያት የግል እርሻዎች ወደ መንግስት እንዲዞሩ ሲደረግ የጥጥ እርሻ ሽፋን ከፍተኛ መነቃቃትና መሻሻል ታይቶበት ነበር፡፡

መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፎች መካከል የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፉ ዋነኛ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በስፋት በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እና ከፓርክ ውጭ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ኢንቨስትመንት መስክ ያለውን አንፃራዊ ጠቀሜታ ታሳቢ በማድረግ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

በአሁኑ ጊዜ ያሉት ነባር እና አዳዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው የሚያመርቱ ከሆነ ከ100 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የተዳመጠ ጥጥ ምርት እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል፡፡

በ2017/18 የምርት ዘመን 110 ሺህ 596 ሄክታር መሬት ላይ ጥጥ በማልማት 69 ሺህ 822 ቶን የተዳመጠ ጥጥ ማምረት ተችሏል፡፡

ሀገራችን ለጥጥ ልማት ተስማሚ የሆነ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዳላት ይነገራል። ይህንንም ከፍተኛ የአቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ሀገራችን የጥጥ ሰብልን ለማልማት ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የኢንዱስትሪዎችን የጥጥ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በሃገር ውስጥ አቅርቦት ለመሸፈን እና ትርፍ ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲያስችል በቀጣይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።

በሀገራችን የጥጥ ልማት ስትራቴጅ ዕቅድ ግቦችን ማሳካት ቢቻል በአማካይ በየዓመቱ 50 ሺህ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ኤክስፖርት በማድረግ ከ100 እስከ 125 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ግኝት ምንጭ መሆን ይችላል፡፡

ባለፉት 5 ዓመታት የጥጥ ሰብል ከእርሻ እስከ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ድረስ ባለው እሴት ሰንሰለት ከ150 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

በቀጣይ በተቀመጠው የ10 ዓመት እቅድ መሰረት ለግማሽ ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የሚገመት ሲሆን ከ100 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የገቢ ምንጭ እንደሚሆን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በግብርናው ዘርፍ የአስር ዓመት ዕቅድ መጨረሻ ላይ የተሻገረ ግብርና ዕውን እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራባቸው ሁሉም የልማት መስኮች እንዲሳኩ በማድረግ ረገድ የጥጥ ሰብል ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በአጠቃላይ ለግብርናው ዘፍርና ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አበርክቶው እጅግ የጎላ ነው።

አዘጋጅ፦ ሰለሞን ደምሰው

ፎቶ፦ ማቲዎስ ተገኝ