አዲስ አበባ፣ መስከረም 15/2019 ዓ.ም (ግብርና ሚኒስቴር) ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የወተት ሀብት ልማትን ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
መድረኩ የወተት ዘርፉን ለማሳደግ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚደረጉ ጥረቶች በተቀናጀና ወጥነት ባለው የኤክስቴንሽን አሰራር ለመፈጸም የሚያስችል ሀገራዊና ወጥ የሆነ የወተት ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት የሚያስችል የምክክር መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ቢሆንም፣ ከእንስሳት ሀብት ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች። ይህንን ክፍተት ለመሙላት የወተት ምርትን ጥራቱንና ደረጃውን አስጠብቆ ለገበያ ማቅረብ እንዲቻል በየደረጃው የሚገኙ የወተት እሴት ሰንሰለት ቁልፍ ተዋናዮችን ወደ አንድ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
የእንስሳት እና አሳ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዚዝ አያለው፣ የወተት ምርትን ጥራቱን እና ደረጃውን አስጠብቆ ለገበያ ለማቅረብ በየደረጃው የሚገኙ የወተት እሴት ሰንሰለት ቁልፍ ተዋናዮችን እውቀት እና ክህሎት ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የተበታተኑ ጥረቶችን ወደ አንድ የጋራ ኃይል በመቀየር ውጤታማ አሰራር መዘርጋት የብልጽግና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ አዚዝ፣ ወጣቶችና ባለሀብቶች በዘርፉ በሰፊው እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችና ተቋማት በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላት በቀጣይ በተለዩ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
