FDRE Ministry of Agriculture

የቡና ልማትን ከጥምር-እርሻ ጋር በማቀናጀት ዘርፈ-ብዙ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ!

እንደ ሀገር የቡና ምርታማነትና ጥራት እየጨመረ በመምጣቱ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እና የአርሶአደሩ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል፡፡

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በማሳደግ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ የቡና ልማታቸውን ከጥምር-እርሻ (አግሮፎረስትሪ) ጋር በማቀናጀት ምርታማነትን፣ የገቢ ምንጭ መፍጠር እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ለማሻሻል እየሠሩ ነው።

ከእነዚህ መካከል አርሶአደር አዲሱ ኪዳኔ ተጠቃሽ ናቸው።

አርሶአደር አዲሱ በጌዲዮ ዞን ገደብ ወረዳ በምትገኝ የሀሎ ባሪቲ ቀበሌ በቡና ልማት ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

‘’የቡና ልማት ለኔ ከቤተሰብ የተቀበልኩት እና ያስቀጠልኩት ትልቁ የልማት ውርሴ ነው’’ የሚሉት አርሶአደር አዲሱ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ የቡና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በመረዳታቸው ያረጁ ቡናዎችን በአዲስ ቡና የመተካት ባህልን እንዳዳበሩ ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሩ አሁን ላይ 9 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘውን የቡና እርሻቸውን በማልማት ላይ ሲሆኑ የጥምር-እርሻ የአመራረት ስርዓትን በመከተል በቡና እርሻቸው ዙሪያ የተለያዩ የጥላና ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ያላቸውን ዛፎች በመትከልና በመንከባከብ ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ ዛፎች ለቡና ተክሎች ተስማሚ የአየር ሁኔታ እንዲፈጠር፣ የአፈሩ ለምነትና እርጥበት እንዲጠበቅ በማገዝ የእርሻው ሥነ-ምህዳር ጤናማነት እንዲጠናከር አስችሏቸዋል፡፡

በተጨማሪም የፍራፍሬ ዛፎች፣ እንሰት እና ሌሎች ጠቃሚ ዕፅዋት የቤተሰቡን የምግብ አቅርቦት ከማሻሻል ባለፈ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲፈጠር ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

የግብርና ባለሙያዎች የቡና ልማት ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን እንዲጠቀሙ የቅርብ ክትትል እያደረጉላቸው እንደሆነ የገለፁት አርሶአደር አዲሱ፣ የሚያለሙት ቡና ጥራትና ብዛት ያለው ምርት እንዲሰጥ ኮምፖስት በማዘጋጀት እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን አርሶአደሩ የቡና ተክሎችን በመንከባከብ፣ ያረጁ ተክሎችን በማደስ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን እና ተገቢውን የጥላ መጠን በመጠበቅ የቡና እርሻቸውን እያሻሻሉ ይገኛሉ።

አርሶአደሩ ከራሳቸው አልፈው ያላቸውን ልምድ ለጎረቤት አርሶአደሮች በማጋራት የቡና ምርትን ከዛፎችና ከሌሎች የእርሻ ምርቶች ጋር በማቀናጀት ዘላቂ የሆነ የእርሻ ሥርዓት እንዲገነቡ ሌሎች አርሶአደሮችን ያበረታታሉ።

ቡናን ከማምረት ባለፈ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ወደ ውጭ የመላክ ትልቅ ህልም እንዳላቸው እና ለዚህም የይዞታ ሰርተፊኬት ባለቤት ለመሆን በቡና የተሸፈነ መሬታቸው እንዲቀየስና እንዲመዘገብ አድርገዋል፡፡

አርሶአደሩ ስራቸውን ከቤተሰብ ጋር በመመካከር እና በመተጋገዝ ለስኬት እንዳደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ማሳያም በገደብ ከተማ ቤት ሰርተው ኑሯቸውን በተሻለ መንገድ እየመሩ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የጭነት መኪና ገዝተው ስራቸውን እያሳለጡ ይገኛሉ፡፡ ለአካባቢው ወጣቶችም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡

የአርሶአደር አዲሱ ልምድ የሚያሳየው አነስተኛ ይዞታ ያላቸው የቡና አልሚዎች የቡና ምርትን ከጥምር-እርሻ ጋር በተገቢው መንገድ በማቀናጀት የምርታማነት እድገት፣ የተሻለ የዛፍ ሽፋን፣ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ማስፋት እና ዘላቂ የእርሻ ሥርዓት በመገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ነው።