ሀገራችን በቆዳና ሌጦ ሀብት ሰፊ አቅም ያላት ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ የግብርና ውጤቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የከብት ቆዳ፣ የበግ እና የፍየል ሌጦ ይመረታል፡፡ ሆኖም በጥራትና በብዛት ተሰብስቦ ለገበያ የሚደርሰው ቁጥር ከሚመረተው አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡
ቆዳና ሌጦ ለኢኮኖሚ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለተለያዩ ባህላዊ አገልግሎቶች እና ለሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ ሃብቱን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡
ስለሆነም በመጪው የአዲስ አመት በዓል በሚከናወን በቅድመ እርድ፣ በእርድ ወቅትና በድህረ-እርድ የሚፈጠሩ የቆዳና ሌጦ የጥራት ጉድለተቶች ላይ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡
በቅድመ እርድ፣ በእርድ ጊዜና ከእርድ በኋላ ለቆዳ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች
ለእርድ የሚቀርበውን እንስሳት በዱላ አለመምታት፣
እንስሳው ለእርድ ሲጣል ከመሬት ጋር አለማጋጨት፣
እንስሳው የሚታረድበትን ቦታ ንፁህ ማድረግ፣
እንስሳው ሲታረድ ደም ተሟጦ እንዲወጣ ማድረግ፣
ቆዳው ሲገፈፍ ቅርፅን መጠበቅና በአሰነዛዘር ወቅት የተፈጥሮ መስመርን ተከትሎ መሰንዘር፣
ቆዳው ሲገፈፍ በቢላ እንዳይበሳ መጠንቀቅ፣
ቆዳው ሲሰበሰብ መሬት ላይ አለመጎተት፣ አለማቆሸሽ፣
ቆዳው ሲሰበሰብ እንዳይበሰብስ መጠበቅ፣
መሬት ላይ አለማድረቅ እና
በፀሃይ መሬት ላይ አለመገድገድ ዋነኞቹ ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በመጨረሻም በዓላትን ምክንያት በማድረግ እርድ በሚፈፀምበት ወቅት አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያሳሰበ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ አመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ እያለ መልካም በዓል እንዲሆን ይመኛል፡፡
ጳጉሜን 5 ቀን 2018 ዓ.ም
ግብርና ሚኒስቴር
