አዳማ፣ ነሐሴ 21/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ዓብይ ኮሚቴ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።

የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ የመሠረተ-ልማት መስክ በርካታ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን በ2018 በጀት ዓመት እንዲሁም በአዲሱ በጀት ዓመት እስካሁን 469 የማህበረሰብ መሠረተ-ልማት ማለትም 123 ት/ቤቶች፣ 62 የሰው እና 15 የእንስሳት ጤና ተቋማት፣ 103 የውሃ ተቋማት፣ 136 የገጠር መንገዶች፣ 25 የመጀመሪያ ደረጃ የገበያ ማዕከሎችና 5 የግብዓት መጋዘኖች ግንባታ ተጠናቅቀው ከ2 ነጥብ 1ሚሊየን ለሚልቁ ስደተኞችና ለስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ፕሮጀክቱ ስደተኞችን ያስጠለሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማዕከል በማድረግ ማህበራዊና ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ ተቀርፆና ፀድቆ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በምዕራፍ ሁለት ክንውኑ በርካታ የማህበረሰብ ተኮር የልማት ስራዎችን በመስራት የስደተኛ ተቀባይና ስደተኛ ማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል፡፡
በያዝነው በጀት ዓመት ስደተኛውንና የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በሚያግዙ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የተሻሻሉ የእንስሳት እርባታ፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የተፈጥሮ ሐብት ልማትና ጥበቃ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል፡፡
የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ፀሐይ እሼቴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የምዕራፍ ሁለት ትግበራውን ከጀመረበት ጥር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቡን እና ስደተኞችን የልማቱ ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።
በመድረኩም የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
