አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ዘርፍ ከባህላዊ የአመራረት ዘዴ ተላቆ ወደ ዘመናዊ፣ በቴክኖሎጂና በመስኖ ላይ የተመሠረተ የግብርና ሥርዓት እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
ይህ የሽግግር ምዕራፍም የዘርፉን ምርትና ምርታማነት፣ የአርሶ አደሩን ገቢ፣ የምግብ ዋስትናን እንዲሁም የሀገርን የኢኮኖሚ ዕድገት በእጅጉ እያጠናከረ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን፣ የአፈር ማዳበሪያን፣ ሜካናይዜሽንንና የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን በማስፋፋት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠራው ሰፊ ሥራ በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል፣ በአርሲ ዞን ዲገሉና ጢጆ ወረዳ በዚህ በ62 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ በኩታ-ገጠም (ክላስተር) ልማት በስፋት እየተከናወነ ሲሆን በአርሲ ዞን በአጠቃላይ 246,435 አርሶ አደሮች በ422,836 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴን በክላስተር እያለሙ መሆኑ ከዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
