የስንዴ ራስ አድርቅ (Fusarium Head Blight) በመባል የሚታወቀው በሽታ በአለም ዙሪያ በስንዴና በሌሎች የብርዕ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ የምርት ቅነሳና የጥራት ችግር የሚያመጣ የፈንገስ በሽታ ነው።
ይህ በሽታ ስንዴን በዋናነት ከሚያጠቁ ፈንገሶች ውስጥ አንዱ ሲሆን ከ17 በላይ በሚደርሱ የተለያዩ የፉዛሪየም ዝርያዎች ለበሽታው መከሰት ምክንያት ናቸው፡፡
ነገር ግን ይህ በሽታ በብዛት ፉዛሪየም ግራሚነረም (Fusarium graminearum) በሚባለው ዝርያ ይከሰታል፡፡ በሽታውም ከምርት ቅነሳ በተጨማሪ የተለያዩ ማይኮቶክስን በመባል የሚታወቁ እንደ ዲኦግዚኒቫሌኖል፣ (Deoxynivalenol (DON))፣ ትራይኮቴሰን (Trichothecene)፣ ኒቫሌኖል (Nivalenol (NIV)) እና ዜራአሌኖን (Zearalenone (ZEN)) የተሰኙ መርዛማ ሻጋታ የሆኑ በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትሉትን የሚያመነጭ ነው፡፡
✍ የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ (Fusarium Head Blight) ምልክቶች እና ልዩ ባህሪያት
👉 በሽታው የሚከሰተው የስንዴው ተክል መዘርዘር/ራስ ማውጣት ሲጀምርና ቀጥሎም ቢጫ አበባ በሚያብብበት ወቅት ነው። ቀጥሎም ፍሬ መሙላት በሚጠበቅበት ወቅት አበባ በጀመረበት የፍሬ አቃፊ /spikelets/ ላይ ድንገተኛ መገርጣት premature bleaching ምልክት ያሳያል።
👉 የበሽታው ምልክትም በስንዴው ራስ እና በልጥፍ አበቢቱ/በፍሬው ላይ የመንጣት/የመገርጣት (Spikelet Bleaching) ምልክት ያሳያል፡፡
👉 ይህም ምልክት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታየው የስንዴ ፍሬውን በሚሸፍነው ክፍል (Spikelets) መሀል ላይ ሲሆን በቀጣይም ወደ ላይ እና ወደ ታች እየሰፋ ይሄዳል፣ ይህም የሚሆንበት ምክንያት በሽታው በዋናነት በአበባ ጊዜ የሚከሰት ስለሆና እና የስንዴ አበባ ደግሞ በተፈጥሮ የሚጀምረው ከመሀል በመሆኑ ነው፡፡
👉 ከፍተኛ እርጥበት በሚገኝ የአየር ሁኔታ ላይም ቀስ በቀስ የስንዴ ፍሬውን በሚሸፍነው ክፍል ላይ ደማቅ ሮዝ ሳልሞን ቀለም (Pink or Salmon-Colored Mold) የፈንገስ /ሻጋታ ምልክት ይታያል፡፡
👉 የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ ለመከሰት በከፍተኛ የአየር ፀባይ ሁኔታ(Weather-Dependent Disease) የሚወሰን ሲሆንእሱምሞቃታማ(Warm) (25–30°C) እና ከፍተኛ እርጥበት (Humid) በአበባ ወቅት ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ወቅት የበሽታው ስርጭት ለመስፋፋት ዝናብና ነፋስን እንደመንቀሳቀሻነት ይጠቀማል፡፡
✍ ምርት ሲሰበሰብም
👉🏽 በበሽታው የተጎዱ ዘሮች ትክክለኛ ቅርፃቸውን በማጣት የተጨማደዱ (Premature Kernel Shriveling) ከመሆን ባሻገር ቀለማቸው ነጭ ወይም ጥቁር እና ቀላል ይሆናሉ። ይህም የሞተ ዘር (Tombstone kernels) በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የምርት መቀነስና ጥራት ችግርም ያስከትላል።
👉🏽 በተጨማሪም በዚህ በሽታ የተጠቃ ዘር የተለያዩ ማይኮቶክሲን እንደ (Deoxynivalenol (DON) ያሉ መርዛማ ነገሮችን በማመንጨት (Production of Mycotoxins) በሰውና በእንስሳት ጤና ላይም ከፍተኛ ችግር ያመጣል።
👉🏽 አንዳንድ ጊዜ የበሽታው ምልክቱ በዓይን ሳይታይ (Hidden Infections) ሰብሉ እስከ ሚሰበሰብ ድረስ በሰብሉ ውሰጥ የሚኖር ሲሆን ይህንንም ክስተት በቤተ ሙከራ (laboratory) ካልተረጋገጠ በስተቀር ማወቅ አይቻልም።
👉🏽 ይህ ፈንገስ የመጀመሪያው ምርት ከተነሳ በኋላ በእርሻ ላይ በሰብሉ ቃርሚያ (Residue Survival) ላይ ይቀመጣል። በተለየ ሁኔታ በበቆሎ እና በስንዴ ቃርሚያ ላይም ይኖራል። ስለዚህ በምክረ ሀሳቡ መሰረት ለሚቀጥለው የምርት ዘመን የሰብል ፈረቃ ማድረግ እና የሰብልን ቃርሚያ ሰብስቦ በአግባቡ ማስወገድ አስፈላጊ ነው።

✍ የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታን (Fusarium Head Blight) መከላከል አስቸጋሪ የሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች
👉🏽 በሽታውን ሙሉ በሙሉ ሊቋቋሙ የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎች በሀገር ውስጥ አለመኖር፣
👉🏽 ስንዴው መዘርዘር ከጀመረበት እስከ ሚጮረቃ ድረስ ባለው የእድገት ደረጃ ውስጥ አየር ንብረቱ ተለዋዋጭ/ተከታታይ ዝናብ፣ሙቀት እና ጭጋጋማ እርጥበት አዘል/ከሆነ የበሽታው አደገኝነት እየጨመረ የሚመጣ በመሆኑ፣
👉🏽 እንደሀገር በባለሙያዎች እና በአርሶ-አደሮች ዘንድ ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ ያለመኖሩ እና የቅድመ-ጥንቃቄ ጉድለት፣
👉🏽 በሽታውን በፀረ-ፈንገስ ርጭት መከላከል/መቆጣጠር ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው በሽታው በአበባ ላይ ከተከሰተ ባሉት ስድስት (ሁለት ጊዜ ርጭት በማካሄድ በመሆኑ) ቀናት ብቻ በመሆኑ የበሽታውን ቁጥጥር ሥራ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ይህም አበባው 50% ቢጫና 50% ነጭ ከለር እከሚሆን ድረስ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡
✍ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ መንገዶች
✍️ የባህላዊ መከላከያ መንገዶች
✍️ በተዘሩ የስንዴ ማሳዎች ላይ
👉🏽 በእርሻ ቁሳቁሶችም ሆነ በመስክ ስራዎች ላይ ጥሩ የማሳ/የቁሳቁስ ንፅህና አጠባበቅ ዘዴዎችን በመጠቀም የዚህ በሽታ አምጪ ፈንገስ መራቢያ አካል (Inoculum) መጠን በመቀነስ የፉዛሪየም ሄድ ብላይት ስርጭትን መከላከል፣
👉🏽 በማሳ ውስጥና ዙሪያ ለበሽታው መራቢያነት የሚያገለግሉ የሳር ዘር የሆኑ አረሞችን እና ሌሎች አስተናጋጅ ተክሎችን ማስወገድ፡፡
👉🏽 በሽታው በአበባው ላይ በተከሰተበት ወቅት የበሽታ አምጪ ተዋህሲያን ሊያሰራጭ ስለሚችል የተለያዩ የእርሻ ስራዎችን በማቆም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
✍ በቀጣይ የምርት ዘመን
👉🏽 ከበሽታው የፀዳ ዘር መጠቀም፣ ቢቻል ቀደም ብሎ የሰብል ቅሬቶችን ማስወገድ፣ እርሻን በጥልቅ ማረስ፣ ትክክለኛ የዘር ወቅት መጠበቅ፣ በመስኖ ለሚያለሙ አካባቢዎች የውሃ አሰጣጥ መርሃ ግብራቸውን ማስተካከልና (በአበባ ወቅት ውሃን በአግባቡ ማጠጣት በተለይ የርጭት ውሃ/sprinkler irrigation አጠጣጥ ዘዴን የምንጠቀም ከሆነ ጥንቃቄ ማድረግ። ነገር ግን በአበባ ወቅት ሰብሉ የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም መሆን አለበት) ከተቻለ ከበሽታው ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ሰብሎች ማፈራረቅ (ከጥራጥሬ ሰብሎች ጋር ከስንዴ ገብስና በቆሎ ውጪ) ጥሩ ውጤት ያመጣል፡፡
✍ ፀረ-ፈንገስ ኬሚካል መጠቀም
ትክክለኛውን የተመዘገበ ፀረ-ፈንገስ ኬሚካል መጠቀም የበሽታውን ስርጭት እንዲሁም የጉዳት መጠን ለመቀነስ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ስለዚህም ውጤታማ የፀረ – ፈንገስ ርጭት ለማካሄድ የርጭት ወቅቱን በደንብ ለይቶ ማወቅ እና በዚህ ወቅት ብቻ ርጭት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሽታው በስንዴው ራስ ላይ ከታየ ወዲያውኑ ርጭት ማካሄድ የሚያስፈልግ ነው፡፡ በተጨማሪም በባለፈው ምርት ዘመን የበሽታው ክስተት በዛ ማሳ ላይ ከነበረ (ስዕል 2(ሀ) ን ይመልከቱ)፡፡ እንዲሁም በሽታው አበባ ማበብ ሲጀምር ከተከሰተ እና የአበባው ቀለም ቢጫ በሚሆንበት ወቅት በጣም ውጤታማ ጊዜ በመሆኑ ርጭት ቢደረግ ይመከራል(ስዕል 2 (ለ) ን ይመልከቱ)፡፡ እንዲሁም 50% አበባው ቢጫና 50% አበባው ነጭ ቀለም በሚሆንበት ወቅትም በስድስት ቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ ርጭት ቢካሄድ በሽታወን መከላከል/መቆጣጠር የሚቻል ሲሆን (ስዕል 2 (ሐ) ን ይመልከቱ ፤ ነገር ግን የስንዴው አበባ ሙሉ ለሙሉ ነጭ ቀለም ሲያወጣ እና የበሽታው ምልክት ፍሬው መሙላት ሲጀምር ላይ ከታየ ርጭት ቢካሄድ በጣም የዘገየ በመሆኑ ውጤታማ አይሆንም፡፡(ስዕል 2 (መ)ን ይመልከቱ)፡፡

ምስል 2፡-የፉዛሪየም ሄድ ብላይት በሽታ የፀረ-ፈንገስ ኬሚካል ትክክለኛ የርጭት ጊዜን የሚያሳይ ስዕል
✍ ማሳሰቢያ፡–
👉🏽 የፀረ -ፈንገስ ርጭት የሚካሄደው በባለፈው ምርት ዘመን የበሽታው ክስተት በነበረባቸው ማሳዎች ላይ እና በአጎራባች ማሳዎች ላይ በሽታው ካለ የፀረ – ፈንገስ ርጭት መካሄድ አለበት በሽታው ባይከሰትም፡፡ ምክንያቱም የበሽታ አምጪ ተዋህሲያን በስንዴ ቃርሚያና በአፈር ውስጥ የህይወት ዑደቱን ስለሚያሳልፍ፣ ስንዴ ዓመቱን ሙሉ (በመኸር፣ በመስኖና በበልግ ወቅቶች) መመረቱና ምቹ የአየር ሁኔታዎች በመኖራቸው ነው፡፡
👉🏽 የስትሮብሊን (Striobin) ምርት የሆኑትን ፀረ-ፈንገሶች ዶን (DON,Deoxynivalenol) otoxins) የተባለውን ማይኮቶክሲን መጠን ስለሚጨምር ፉዛሪየም ሄድ ብላይትን ለመቆጣጠር መጠቀም አይመከርም፡፡ በመሆኑም ፉዛሪየም ሄድ ብላይት በሽታን ለመከላከል/ለመቆጣጠር በዋናነት የተመዘገበውን (በንግድ ስሙ ፉዛሮ 400SC/Fuzaro 400 SC) በcommon name ደግሞ ebuconazol+Prothioconazole የተባለውን ፀረ – ፈንገስ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ርጭት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡
👉🏽 በፀረ-ፈንገሱ መያዣ ላይ ያለውን የአሠራርና ጥንቃቄ መመሪያ በሚገባ መከተል የሚሉት በዋናነት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡
#ከማምረትበላይ #BeyondProduction
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት👇
📌ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et
📌ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/MoAEthiopia
📌ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia
📌ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews
📌ቲዊተር፦ https://x.com/MoA_Ethiopia
📌ሊንክድኢን፡- https://shorturl.at/7O6cs
📌ቲክቶክ፦ http://www.tiktok.com/@moaethiopia