በግብርናው ዘርፍ እስካሁን ለተመዘገቡ ስኬቶችና በቀጣይ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ የስርዓተ-ጾታ አካታችነት የማይተካ ሚና አለው፡፡ የስርዓተ-ጾታ ተግባራዊ መማማሪያ ዘዴ (Gender Action Learning System/GALS) ወንድና ሴት የቤተሰብ አባላት ከቤት ውስጥ ስራ እስከ ማሳ ያለውን ስራ በመደጋገፍ፣ በመመካከር፣ እኩል በመወሰን፣ አብሮ በማቀድና በመተግበር የጋራ አላማቸውን የሚያሳኩበት ነው፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከንባታ ጠምባሮ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ የቡጋሜሴና መንደር ለበርካታ አመታት የቤት ውስጥ ስራ ለሴቶች፣ የማሳ ደግሞ ለወንዶች የተሰጠ አድርገውት ቆይተዋል፡፡ የአካባቢው ሴቶች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ስራው የአባወራ ነው በማለት ህልማቸውን እውን ማድረግ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡

አሁን ግን በቡጋሜሴና መንደር ሴቶችን እንደ አንድ የግብርናው ልማት አካል አድርጎ በመያዝ በግብርናው ምርታማነት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ ባልና ሚስት ከቤት እስከ ማሳ እንዲተጋገዙና የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት ሚና ከፍ ለማድረግ እንዲቻል የስርዓተ-ጾታ በተግባር የመማማሪያ ዘዴ በተሳትፏዊ የግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም አማካኝነት እየተተገበረ ነው፡፡

የስርዓተ-ጾታ ተግባራዊ የመማማሪያ ዘዴ በግብርናው መስክ ብቅ ማለቱ በቡጋሜሴና መንደር የነበረውን የስራ ልዩነት ታሪክ ማድረግ ችሏል፡፡ በዚህ ተግባራዊ የመማማሪያ ዘዴ ቤተሰቦች ራዕያቸውን በማስቀመጥ፣ በማቀድ፣ በመተግበር እና ስኬትን በጋራ በማምጣት ህልማቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡ በቤተሰብ መካከልም የመተጋገዝ ባህል ጠንክሯል፡፡

አርሶ አደሮችን በተለይም ሴቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ያለው ሌላኛው ተግባር ደግሞ የአርሶ አደሮች የመስክ ትምህርት ቤት ሲሆን በክልሉ ሀዲያ ዞን ምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ሰጴራ መንደር የሚገኙ አርሶ አደሮች በተግባር በመማር ምርታመነታቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ፡፡ አርሶ አደሮች በመስክ ትምህርት ቤቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመቀበል እና የአየር ንብረትን የሚቋቋም ግብርናን በመተግበር የኤክስቴንሽን አገልግሎትን እያጠናከሩ ይገኛሉ፡፡
አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶ፡- ጌታቸው ምትኩ
