FDRE Ministry of Agriculture

የስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ሞዴል መንደር አስፈላጊነት!

በሀገራችን የሥርዓተ-ምግብ መጓደል በቂ የምግብ አቅርቦትና ተደራሽነትን ያለማረጋገጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የግብርና ምርት የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘትና የስብጥር ሁኔታ እንዲሁም የቤት ውስጥ አመጋገብን ስርዓትንም ይጨምራል።

ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎችም እኩል በሚባል ደረጃ በስርዓተ-ምግብ መጓደል ችግር እየተጎዱ ስለሆነ የማህበረሰቡን ምግብና ስርዓተ ምግብ ለማሻሻል ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሆኗል፡፡

የስርዓተ-ምግብ መጓደል ችግር መፍቻ ስልት ከሆኑት ተግባራት መካከል አንዱ የስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ሞዴል መንደር መመስረት ሲሆን፤ ዋናው ጽንሰ ሃሳብ ደግሞ በሚመሰረተው መንደር ውስጥ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት የስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ተግባራትን ማለትም በምግብ ንጥረ-ነገር ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦች አቅርቦት፣ ተደራሽነት እና የተሰባጠረ አመጋገብ እንዲሁም የአካባቢና የግል ንፅህና አጠባበቅ፣ የገቢ ማስገኛ ስራዎች እና የሴቶች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የምግብና ስርዓተ ምግብ ጽ/ቤት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተመረጡ ቦታዎች ላይ ላለፉት ሶስት አመታት የስርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና ሞዴል መንደር በመመስረት ሲተገበር ቆይቷል፡፡

ይህንም ለመተግበር ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የባህሪ ለውጥ አምጪ ስራዎችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ የመማማሪያ ማዕከልና ልምድ ለመጋራት የሚያስችል ሞዴል መንደር መመስረት ተችሏል፡፡

ሞዴል መንደሩ ከተመሰረተባቸው አከባቢዎች አንዱ በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ትርፌ ወተሬ ቀበሌ ወተራ ሞዴል መንደር አንዱ ሲሆን በመንደሩ አንድ ማሰልጠኛ ማዕከልና ሞዴል አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡

በትርፌ ወተራ ቀበሌ የሚገኘው የወተራ ሞዴል መንደር ነዋሪ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል አንዱ አርሶ አደር ኑሪ ኤሌሞ ናቸው፡፡ በፊት ምርቱ ቢኖርም አጠቃቀሙን ባለማወቃቸው በቀን ውስጥ አሰባጥረው የተመጣጠነ ምግብ አይመገቡም ነበር፡፡ አሁን በጓሮአቸው አትክልቶችን አሰባጥረው እንደ ጎመን፣ ቀይ ስር፣ ካሮት እንዲሁም ከፍራፍሬ አፕል እና ሙዝ ያለማሉ፡፡

እነዚህን ከእንስሳት ተዋጾኦ ጋር አሳባጥረው ምግባቸውን በማዘጋጀት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተመጣጠነ ምግብ ይመገባሉ፡፡ አርሶ አደር ኑሪ እንደሚሉት በፊት ስንዴ፣ ጤፍ፣ ቦቆሎና መሰል ሰብሎችን ቢያለሙም አመጋገብ ላይ ችግር እንደነበር ጠቅሰው አሁን የስርዓተ ምግብ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በቤታቸው የአመጋገብ ስርዓታቸው ተቀይሯል፡፡ በዚህም ስድስቱን ዋና ዋና የምግብ ንጥረ ነገሮችን ከሚያስገኙ ምርቶች ምግብ ተዘጋጅቶ መላ የቤተሰባቸው አባላት ይመገባሉ፡፡

በዚህም ልጆቻቸው ጤነኛ፣ ደስተኛና በትምርታቸውም ውጤታማ መሆን ችለዋል፤ ከቤት ቀለብ የተረፈውን የጓሮ አትክልትና ሌሎች ምርቶች በመሸጥ ጥሩ ገቢ እያገኙ ነው፡፡

በመጨረሻም አርሶ አደር ኑሪ በራሳቸው ቤተሰብ የመጣውን ለውጥ በመመልከት፣ ምርታማም በመሆናቸው ልምዱ ከመንደራቸው ባለፈ ለመላ ኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ቢስፋፋ ምኞታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡