FDRE Ministry of Agriculture

የስልጤ ዞን ዘንድሮ ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች 65% ለማስመረቅ እየሰራ ይገኛል፡፡  

የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታመነት በብዙ መንገድ ይገለፃል፡፡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የምግብ ክፍተትን ከመሙላት ባሻገር የበርካታ አርሶአደሮችን ኑሮ ቀይሯል፡፡ ፕሮግራሙ በርካታ ተጠቃሚዎች የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ሀብት እንዲያፈሩ ያስቻለ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በማህበረሰብ ስራዎች የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው እንዲለሙ በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ጉልህ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡

ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውጤት ካመጣባቸው ዞኖች መካከል የስልጤ ዞን አንዱ ነው፡፡  የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ወሲላ አሰፋ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም አርሶ አደሮች (በፕሮግራሙ የታቀፉት) በልተው እንዲኖሩ የምግብ ክፍተታቸውን ከመሙላት ባሻገር በተጠቃሚዎች ኑሮ ላይ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን በሰራቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች  የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው በመልማታቸው  ምቹ የንብ ማነቢያና የመኖ ምንጭ እንዲሁም በከብት  እርባታና ማድለብ ስራ ላይ ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ  ለግብርና  ምርትና ምርታማነት መጨመር የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከቱን ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

ሰጪ እጅ ከላይ፣ ተቀባይ እጅ ከታች በመሆኑ ሁልጊዜ መቀበል እንደሚያዋርድ ወ/ሮ ወሲላ ጠቅሰው ሁሉም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገር የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዘንድሮ በዕቅዱ መሰረት ሰርተው ከሚደገፉ ተጠቃሚዎች መካከል 65 በመቶው ሲመረቁ (ሲሸጋገሩ) እንደ ዞን የድህነት መጠንም ይቀንሳል ብለዋል፡፡

በስልጤ ዞን አሁን ካሉት 43,465 የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ውስጥ የማህበረሰብ ስራ ሰርተው የሚደገፉ ተጠቃሚዎች ቀጥር 37,273 ሲሆን ከነዚህ ተጠቃሚዎች ዘንድሮ ስልሳ አምስት በመቶ (65%) የሚሆኑትን ለማስመረቅ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዋናነት በአስተሳሰብ ላይ መሰራት ነው ያሉት በስልጤ ዞን የሳንኩራ ወረዳ የልማታታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የአግሪ ቢዝነስ ባለሙያ አቶ እንድሪያስ ክንፈ ብድር ለሚወስዱ ተጠቃሚዎች በህይወት ክህሎት፣ በገበያ ትስስር፣ በአዋጭ ንግድ አዘገጃጀት እና በሂሳብ አያያዝ ላይ በ4 ዙር ሰፋፊ የተጠናከረ ስልጠና በመስጠታቸው ከግንዛቤ መዳበር የተነሳ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ስኬታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የልምድ ልውውጥ በማድረግ  ፍላጎትና ተነሳሽነትን በተጠቃሚ አርሶአደሮች ውስጥ በመፍጠር ጥሩ ተሞክሮዎችም እንዲስፋፉ ማስቻሉን አቶ እንድሪያስ ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ በቦኖሻ ቀበሌ ውስጥ በገነባው ቦኖሻ ችግኝ ጣቢያ በኩል ለተጠቃሚ አርሶአደሮች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ በችግኝ ጣቢያው የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያና የቡና ችግኞችን በማፍላት በአስራ አምስቱም የወረዳ ቀበሌዎች ውስጥ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ችግኞቹን በነጻ ያቀርባል፡፡ ተጠቃሚዎቹም በየጓሯቸው እያለሙ ጥሩ ገቢ እያገኙ ነው፡፡

አርሶአደር አምዳላ ከሊል በሳንኩራ ወረዳ የረግዲና ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከመታቀፋቸው በፊት ምንም ነገር አልነበራቸውም፤ የድሃ ድሃ ነበሩ፤ የቀን ስራ እየሰሩ ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ በፕሮግራሙ ከታቀፉ በኋላ የማህበረሰብ ስራ እየሰሩ  በሚያገኙት ክፍያ የቤተሰባቸውን የምግብ ክፍተት መሙላት፣ የገጠር ገንዘብና ቁጠባ ህ/ሥ/ማህበር አባል በመሆን ከሚያገኙትም ላይ መቆጠብ ጀመሩ፡፡  ምቹ አጋጣሚውን በመጠቀም 4,000 ብር ተበድረው 1,000 ብር በመጨመር 1 የሀገር ውስጥ ዝርያ  ጊደር  በ5,000 ብር ገዙ፤ ጊደሯን  አሳድገው በ20 ሺህ ብር  በመሸጥ ምርጥ የወተት ላም ዝርያ በ35 ሺህ ብር ገዙ፡፡  ብድሩንም መልሰው ሁለተኛ የወተት ላም ገዝተው በማርባት  ጥሩ ገቢ እያገኙ ነው፡፡

አሁን 2 ላሞች፣ 2 ጥጆች፣ 4 ፍየሎች እና 1 አህያ አላቸው፡፡ ባላቸው ግማሽ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይም የተለያዩ ፍራፍሬ፣ ቡናና ሌሎች ሰብሎችን አልምተው ገቢ ያገኛሉ፡፡ ባለ 52 ዚንጎ ቆርቆሮ ቤት በ290 ሺህ ብር ሰርተው ከአልጋ ጀምሮ አስፈላጊ የቤት እቃዎችን አሟልተው ጥሩ ኑሮ እየኖሩ ይገኛሉ፡፡

አርሶአደር አምዳላ በባለሙያ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የራሳቸውንም ጥረት አክለው እዚህ መድረሳቸውንና  ወደ ፊት እነዚህን ስራዎች አጠናክረው ለመቀጠል  እቅድ እንዳላቸው ጠቅሰው በዚህ ዓመት ለመመረቅ ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡

አርሶአደር ከማል ኦበቶ ሌላኛው የረግዲና ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከታቀፉ 10 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ “በፊት አስካፊ ድህነት ውስጥ ነበርኩ፤ እንኳን ልጆች ማስተማር ይቅርና በልቶ ማደርም መከራ ነበር፤  በፕሮግራሙ ሳልታቀፍ ትንሽ ብቆይ እኔም ቤተሰቤም አንኖርም ነበር፡፡ በፕሮግራሙ ከታቀፍን በኋላ በልተን መኖር ችለናል፡፡ ልጆቼንም በአግባቡ አስተምራለሁ፤ የቤተሰብ ጥሪት በመገንባትም ጥሩ ኑሮ እንኖራለን፤” ብለዋል አርሶአደር ከማል፡፡

አርሶአደር ከማል ኦበቶ የማህበረሰብ ስራ ሰርተው ከሚያገኙት ክፍያ በጊዜ ነበር መቆጠብ የጀመሩት፡፡ ጎን ለጎን 10 ሺህ ብር ተበድረው የነበራቸውን በርበሬ በ2,000 ብር በመሸጥ  በ12 ሺህ ብር  1 ወይፈን ገዝተው ማደለብ ጀመሩ፤ አደልበውም በ25 ሺህ ብር ሸጡ፡፡ በሬ በመግዛት አደልበው የመሸጥ ስራውን ቀጠሉበት፤  አሁን 1 በሬና 1 ወይፈን እያደለቡ ናቸው፡፡ ጎን ለጎን ፍየልና ዶሮ ያረባሉ፤ 5 ፍየሎችና 8 ዶሮዎች አሏቸው፡፡ ከዶሮዎቹ የሚያገኙትን የእንቁላል ምርት ከቤተሰብ ፍጆታ የሚተርፈውን ሽጠው ገቢ ያገኛሉ፡፡

ዛሬ በከተማ የመኖሪያ ቤት ገንብተው በማከራየት በየወሩ ገቢ ያገኛሉ፡፡ እርሻ መሬት ተኮናትረው በርበሬ በማልማት ከድህነት ለመውጣት የራሳቸውንም ጥረት አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ ባላቸው 1 ጥማድ ተኩል የእርሻ መሬት ፕሮግራሙ በነፃ የሚያቀርባቸውን ችግኞችን በመጠቀም ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ እና ቡና አልምተዋለል፡፡ ቡና እስከ 2 ኩንታል ለገበያ ማቅረብ ችለዋል፡፡ አርሶአደር ከማል ዘንድሮ ከገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ለመመረቅ ዝግጁ ሆነዋል፡፡

ዘጋቢ፡-  ሸምሱዲን ዩሱፍ

ፎቶግራፍ፡- ያሬድ አሰፋ