FDRE Ministry of Agriculture

የሴቶች አቅም ማጎልበትና የሥርዓተ-ጾታ ሽግግር ፕሮጀክት የሴት አርሶአደሮች እኩልነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው

ሐዋሳ፣ ሰኔ 5/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ የአብይ ኮሚቴ አባላት በሲዳማ ክልል የተከናወኑ የተግባር ስራዎችን በመጎብኘት የሴቶች አቅም ማጎልበትና የሥርዓተ-ጾታ ሽግግር ፕሮጀክት አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ፕሮጀክቱ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እኩልነት ለማረጋገጥ ስልታዊ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን በዚህም በሴቶች የሥራ ጫና ቅነሳ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በገበያ ትስስር ዙሪያ አበረታች ለውጦችን አስመዝግቧል።

በተለይም በሲዳማ ክልል በሼበዲኖ ወረዳ የተተከለው የእንሰት መፍጫ ማሽን የሴቶችን ጊዜና ጉልበት የቆጠበ ሲሆን ጎን ለጎን ከተረፈ ምርት ጌጣጌጥ በመሥራት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ አግዟል።

ፕሮጀክቱ በአቮካዶ፣ ሽንኩርትና በቲማቲም እንዲሁም በእንስሳትና ዓሳ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ሲሆን የአቮካዶ ማቀዝቀዣ፣ የአቮካዶ መቁረጫ እና የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ለምርታማነት እድገት እገዛ አድርጓል።

የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ለማረጋገጥ ደግሞ በየመንደሩ በውይይት ቡድኖች አማካኝነት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመሥራቱ ሴቶች በንብረታቸውና በቤት ወጪ ላይ ከወንዶች ጋር ተወያይተው እንዲወስኑ እያስቻለ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ሞዴል ሴት አርሶአደሮችን በማፍራት ረገድ እያሳየ ያለው አፈጻጸም አመርቂ በመሆኑ ለቀጣይ የፕሮጀክቱ ስኬት የአቅም ግንባታና የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

ፕሮጀክቱ የሴቶችን ሕይወት ለመቀየርና ውጤታማ ሞዴል ሴት አርሶአደሮችን ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምሩ ሞኬ ፕሮጀክቱ በክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥና አርሶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ገነት አብደላ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የአርሶአደሩን የቴክኖሎጂ አተገባበር አቅም ያሳደገ መሆኑን አንስተዋል።