——————
ኢትዮጵያ የጥጥ ሰብልን በማምረት በርካታ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት ስትሆን ጥጥን በሰፋፊ እና የተሻሻለ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማምረት የተጀመረው በ1960ዎቹ ሚቼልኮት በተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ እንደነበር መዛግብቶች ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ የጥጥ ልማቱም እየተስፋፋ ሄዶ ሽፋኑ እስከ 140 ሺህ ሄክታር ደርሶ ነበር፡፡ ከ1974 ዓ.ም ወዲህ የግል እርሻዎች ወደ መንግስት እንዲዞሩ የተደረገ ሲሆን ይህም በጥጥ ሽፋን ላይ ከፍተኛ መነቃቃትና መሻሻል እንዲፈጠር አደረገ፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፎች መካከል የጨርቃጨርቅና ስፌት ዘርፉ ዋነኛ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በስፋት በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እና ከፓርክ ውጭ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንቨስትመንት መስክ ያለውን አንፃራዊ ጠቀሜታ ታሳቢ በማድረግ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

በሃገራችን የጥጥ ልማት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አንዱ ነው፡፡
የጋሞ ብሄረሰብ በሀገራችን ከሚታወቅበት ሀገር በቀል እውቀት ውስጥ አንዱ የሸማ ሥራ ጥበብ ነው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በሀገራችን በሸማ ሥራ ጥበብ ከሚታወቁ ጥቂት ማህበረሰቦች አንዱ ጋሞ መሆኑም የተለያዩ ድርሳናት ያትታሉ፡፡
የሸማ ሥራ በሀገራችን መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከረጅም ጊዜ አንስቶ በጋሞ ዶርዜ አካባቢ የሸማ ሥራ ይተገበር ነበር፡፡ ለዚህም ዋናው ግብዓት ደግሞ ጥጥ ነው፡፡
በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቆላሼሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ይታሹ በላይነህ በኦርጋኒክ የጥጥ ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶአደር ናቸው፡፡ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ የጥጥ ልማት ስራ እንደጀመሩ የሚናገሩት እኚሁ አርሶአደር በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ከሚያመርቱት ጥጥ እስከ 200 ኩንታል ምርት ያገኛሉ፡፡

ወ/ሮ ይታሹ በላይነህ ግብርና ሚኒስቴር ከሶሊዳሪዳድ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የሰጣቸው የኦርጋኒክ ጥጥ ልማት ስልጠና ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው ይመሰክራሉ፡፡
በቀጣይም የኦርጋኒክ ጥጥ ልማት አሁን ካላቸው ማሳ በተጨማሪ በማስፋፋት እና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ይናገራሉ፡፡
የገበያ ትስስሩ ወጥነት ኖሮት የሚያመርቱት ኦርጋኒክ የጥጥ ምርት ከማሳቸው ቀጥታ ወደ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች እንዲደርስ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል አስፈላጊው ስራዎች ቢሰሩላቸው የበለጠ ውጤታማ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አርሶአደር አበራሽ አሮ ደግሞ በጋሞ ዞን ም/አባያ ወረዳ ፓራጎሳ ቀበሌ በጥጥ ልማት ላይ የተሰማሩ ሴት አርሶአደር ሲሆኑ አካባቢያቸው ለጥጥ ልማት ምቹ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ያለ ጥጥ መኖር አልችልም ያሉት እኚሁ አርሶአደር አሁን ላይ የሚያመርቱት ኦርጋኒክ የጥጥ ምርት ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠላቸው ይገኛል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማትን ምርታማነት በማሳደግ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የግብዓት ፍላጎት ለማሟላት በዘርፉ ከተሰማሩ የልማት አጋር አካላት ጋር በመተባበር የባለሙያዎችን እንዲሁም የአምራቹን አርሶአደርና ከፊል አርበቶአደሮችን የማምረት አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፈር፡- ያሬድ አሰፋ
