ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ የአፈር ጤንነት እና ለምነት ቴክኖሎጂዎችን በአርሶ/አርብቶ አደሩ ለማስረፅ የማስተዋወቅ እና የማስፋፋት ስራዎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ለአብነትም የራይዞቢያ ሕየወ ማዳበሪያን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን በማዳበሪያው አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ ማኑዋል ተዘጋጅቶ አርሶ አደሩ እየተጠቀመበት ለምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የራይዞቢያ ሕየወ ማዳበሪያ የጥራጥሬ ሰብሎችን ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያገለግል የተፈጥሮ ግብዓት ነው። “ራይዞቢያ ሕየወ ማዳበሪያ” የሚለው ቃል “Rhizobium bio-fertilizer” ከሚለው የእንግሊዘኛ ቃል በቀጥታ የተወሰደ ነው፡፡

ትርጓሜውም ሕይወት ባላቸውና በተለያዩ ውጤታማ የራይዞቢያ ባክቴሪያዎች እና ተሸካሚ ቁስ የሚዘጋጅ (ሕየወ ቅምር) ሆኖ የጥራጥሬ ዘር ላይ ታሽቶ በሚራዘምበት ጊዜ ባክቴሪያዎች ከሰብሉ ጋር በሚፈጥሩት መልካም መስተጋብር አማካኝነት በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ናይትሮጂን አቀናብሮ ዕፅዋት በሚጠቀሙበት መልክ በማቅረብ የጥራጥሬ ሰብሎች ዕድገትና ምርታማነትን የሚያሻሽል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ማዳበሪያው በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን የአፈር ጤንነትና ለምነትን ያሻሽላል፤ የጥራጥሬ ሰብሎችን ዕድገት፣ የፕሮቲን ይዘትና ምርታማነትን ያሻሽላል፤ ለኬሚካል ማዳበሪያዎች ግዥ የሚውል የውጭ ምንዛሬን ይቀንሳል፤ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ምርትን ለማግኘት ማስቻሉ ከበርካታ ጥቅሞቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የራይዞቢያ ሕየወ ማዳበሪያ ሕይወት ያላቸው ራይዞቢያ የተባሉ ባክቴሪያዎችን በውስጡ የያዘ ስለሆነ በማጓጓዝም ሆነ በአከመቻቸት ሂደት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡
ለአገልግሎት የምንጠቀመው የራይዞቢያ ሕየወ ማዳበሪያ ህጋዊ በሆኑ አምራቾች መመረቱን እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ እና የመጠቀሚያ ጊዜው ያላለፈ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

የማዳበሪያው አከፋፋይ፣ ቸርቻሪ፣ አቅራቢ እና ተጠቃሚ የማከማቸት ስራው ውጤታማነቱን እንዳይጎዳ በጥንቃቄ ሊከናወን የሚገባ ሲሆን በጣም ሞቃት የሆነ አካባቢ ወይም ክፍል ከሆነ በእርጥብ አሸዋ በተሞላ የሸክላ ማሰሮ ውስጥ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡

የራይዞቢያ ሕየወ ማዳበሪያ ቅምር በዱቄት ወይም በፈሳሽ መልክ ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም በሀገራችን ተዘጋጅቶ የሚቀርበው የራይዞቢያ ሕየወ ማዳበሪያ በድንጋይ ከሰል የተዘጋጀ ነው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የማዳበሪያው አምራቾች የምርታቸውን የአጠቃቀም መመሪያዎች ስለሚያካትቱ ተጠቃሚዎች መመሪያውን መመልከትና መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዘጋጅ፡- ዮሐንስ ደመቀ
