FDRE Ministry of Agriculture

የሩዝ ልማትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ሩዝ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም የውጭ ሀገር ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ አቅም ያለው ምርት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በኢትዮጵያ የሩዝ ልማት ትራንስፎርሜሽን ላይ ግብርና ሚኒስቴር ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ባለከድርሻ አካላት በተገኙበት የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ እንደተናገሩት ሩዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የገቢ ምንጭን ለማሳደግ በተጨማሪም የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት አቅም ያለው አስፈላጊ ምርት ነው።

ይህንንም በመገንዘብ መንግሥት ለሩዝ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱንና በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ሚንስትር ዴኤታው ገልዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በመንግሥት ተቋማት፣ በአርሶ አደሮች፣ በምርምር ማዕከላት፣ በልማት አጋሮች እና አጠቃላይ በግሉ ዘርፍ በጋራ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በሀገራችን የሩዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቴክኒክና ፋይናንስ ድጋፍ፣ በምርምር ትብብር እና በአቅም ግንባታ በኩል የልማት አጋሮቻችን ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።

በመድረኩም የኢትዮጵያ የሩዝ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ለስትራቴጂካዊ አጋርነት እና ኢንቨስትመንት ያለው አስፈላጊነት እንዲሁም የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ለሩዝ ልማት ያደረገው አስተዋፅዖ ላይ ትኩረት ያደረጉ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በዚህም የውይይት መድረክ የሚኒስቴር መ/ቤቱ፣ የተጠሪ ተቋም እንዲሁም የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *