FDRE Ministry of Agriculture

የምግብ ደህንነትና ጥራት እና የድህረ-ምርት አያያዝ ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት‼️


የምግብ ደህንነትና ጥራት እንዲሁም የድህረ-ምርት አያያዝ ተግዳሮቶች በሀገራዊ ልማት፣ በምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትና ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡


ችግሮቹን ከመሰረቱ ለመፍታት በግብርና ሚኒስቴር በምግብና ስርዓተ-ምግብ ጽ/ቤት አስተባባሪነት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሰባት አመት የትግበራ ጊዜ ያላቸው (2024-2030) ሶስት ስትራቴጂዎች (ብሔራዊ የምግብ ደህንነትና ጥራት ለተቀዳሚ የግብርና ምርቶች፣ ብሔራዊ የድህረ-ምርት አያያዝ እና ብሔራዊ የስርዓተ-ምግብ ተኮር አግሪፉድ ሲስተም ስትራቴጂዎች) ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡


ለእነዚህ ስትራቴጂዎች መዘጋጀት ዋና መነሻዎች


👉 የምግብ ደህንነትና ጥራት


የምግብ ደህንነት በኢትዮጵያ ሃገራዊ ልማት ላይ ትልቅ እና አሳሳቢ ፈተና ሲሆን በህብረተሰብ ጤና፣ ንግድ እና የምግብ እና ስርዓተ-ምግብ ዋስትና ላይ ትልቅ ተጽእኖ አለው፡፡


ከሃገር ውስጥና ከውጭ ንግድ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ በዓመት ከ723 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምናጣ የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ተቋም ጥናት ያሳያል።


ችግሩም በዋነኝነት በረቂቅ ተዋህስያን የሚከሰት ሲሆን የአፍላቶክሲን እና የኬሚካል ቅሪቶች በሚያደርሱት ጉዳት አማካኝነት እንደሆነም ጥናቱ ያሳያል፡፡


ከነዚህ ተግዳሮቶች በተጨማሪ ህብረተሰቡ የምግብ ደህንነትና ንፅህና አጠባበቅ ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛነት፣ ጊዜ ያለፈባቸው የህግ ማዕቀፎች፣ በቂ የገንዘብ ድጋፍ አለማድረግ እና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት የምግብ ደህንነት ቀውሱን የበለጠ አባብሶታል።


👉 የድህረ ምርት አያያዝ


በሀገር ደረጃ በኢኮኖሚ፣ በምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትና ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ሲታይ በሰብል ከሚመረተው ምርት ከ20-30 በመቶ፣ በሆርቲካልቸር ከ30-50 በመቶ እንዲሁም በእንስሳት ምርት እስከ 40 በመቶ ብክነት እንዳለ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በምግብ አቅርቦትና ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡


ይህ ብክነት በምግብና ስርዓተ-ምግብ ዙሪያ የንጥረ-ነገር ይዘት ብክነት ስለሚያስከትል የመቀንጨርን፣ የመቀጨጭንና ከክብደት በታች መሆኑን እንዲሁም የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ላይ ተፅእኖ ከማሳደሩም ባሻገር የድህረ-ምርት አያያዝ ለምግብ ደህንነትና ጥራት አስተዋጽዖ ስለሚያደርግ በአግባቡ ካልተተገበረ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚያጋልጥ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።


እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የሚረዱ መፍትሄዎች በስትራቴጂዎቹ የተቀመጡ ቢሆንም እነዚህን ለመተግበር እውቀትና ክህሎት ስለሚያስፈልግ አንዱ የስትራቴጂዎቹ የትኩረት አቅጣጫም በየደረጃው የአስፈጻሚውንና የፈጻሚውን አቅም መገንባት፣ ስልጠና መስጠት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራትና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶና አርብቶ አደሮች ማስተዋወቅን ያካትታል።


ይሀንን ለማስፈጸም እና ስትራጂዎቹን በየደረጃው መተግበር እንዲቻል ሀገር አቀፍ የሆነና ዋና ዋና የግብርና ምርቶችን ያካተተ የስልጠና ማኑዋል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በበላይ አመራሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የማዘጋጀት ስራም ሲሰራ የቆየ ሲሆን ይህንንም መሰረት በማድረግ የአሰልጣኞች ስልጠና በ10 ክልሎች ላይ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡


የስልጠናው ዋና ዓላማም የአርሶ/አርብቶ አደሩን በምግብ ደህንነትና ጥራት እንዲሁም በድህረ-ምርት አያያዝ ላይ እውቀትና ክህሎታቸውን በማሳደግ ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ ምርትን በማምረትና የምርት ብክነትን በመቀነስ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የምግብ ደህንነትን ማሻሻል ነው።


ታህሳስ 2018 ዓ.ም
ግብርና ሚኒስቴር