FDRE Ministry of Agriculture

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (Food System Resilience Program) በግብርና ሚኒስቴር ከሚሰሩ ፕሮግራም እና ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን በዓለም ባንክ በጀት የሚደገፍ ነው፡፡ የፕሮግራሙ ትግበራ ዘመን እ.አ.አ ከ2022 እስከ 2029 ሲሆን የግብርና ዕድገት ፕሮግራም (AGP) I እና II ስኬቶችን በማስቀጠል የሀገሪቷን የምግብ ስርዓት ለማጠናከር ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ፕሮግራም ነው፡፡
ፕሮግራሙ የምግብ ስርዓትን የማሻሻልና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አቅምን የመጨመር ዓላማን ያነገበ ሲሆን በአስር ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በ183 ወረዳዎች ውስጥ በ4,301 ቀበሌዎች እየተተገበረ ነው፡፡ እንደ ሀገር 4.1 ሚሊዮን አባ/እማ ወራዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡
የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በዋናነት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የእሴት መጨመርን እና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡ በዚህም የአነስተኛ ባለይዞታ አርሶአደሮችን ገቢ በመጨመር፣ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትናን እና ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በአራት ቁልፍ ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን እነሱም ከነንዑሳን ክፍሎቻቸው ጭምር የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. የግብርና አገልግሎትና የፈጠራ ስርዓትን ማሻሻል
    1.1. የግብርና አገልግሎት ቅልጥፍናን እና ተደራሽነትን ማሳደግ
    1.2. የግብርና ቴክኖሎጂን ማመንጨት እና የምርምር ስርዓትን መለወጥ/ማዘመን
  2. የአነስተኛና የጥቃቅን መስኖ መሰረተ-ልማትን ማስፋፋት
    2.1. የአነስተኛ ይዞታ አርሶአደሮች መስኖ መሠረተ-ልማት መገንባት
    2.2. የመስኖ ውሃ አያያዝ እና የመስኖ መሠረተ-ልማት አስተዳደር
  3. የገበያ ማዕከላትንና አነስተኛ ድልድዮችን መገንባት
    3.1. የገበያ ልማት
    3.2. በቡድን የተደራጁ አንተርፕራይዞችን ማጠናከር/ማቋቋም
  4. ለሥርዓተ ምግብና ለፕሮግራም አሰተዳደር አሰቻይ ሁኔታዎችን ማሻሻል
    4.1. የፕሮግራም አስተዳደርና የፕሮግራም ክትትል፣ ግምገማ እንዲሁም ትምህርት ናቸው፡፡
    እነዚህ ክፍሎች ተሰናስለው አካታች የምግብ ስርዓትንና አቅምን ይበልጥ ለመገንባት ምቹ ሁኔታን በስፋት ይፈጥራሉ፡፡
    በአጠቃላይ፣ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በሰብል፣ በሆርቲካልቸር፣ በእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት እንዲሁም በአነስተኛ የመስኖ አወታሮች ግንባታ፣ በገበያ ማዕከላትና አነስተኛ ድልድዮች ግንባታ እና በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ የግብርናውን ሽግግር እያፋጠነ ይገኛል፡፡