አዳማ፣ ሚያዝያ 06/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ከአትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባባር “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) በፓናል ውይይቱ ባሰተላለፉት መልዕክት ባለፉት የለውጥ አመታት በግብርናው ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች በምግብ ራስን መቻል፣ ተኪ ምርትን ማምረት፣ ወደ ዉጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ምርታማነት ማሳደገ እና በግብርናው ዘርፍ የስራ ዕድል በመፍጠር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከተረጅነት ወደ ትርፍ አምራችነት እንዲቀየሩ በማድረግ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡
“ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉአላዊነት እና ክብር” በሚል ርዕስ ለፓናል ውይይቱ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
በመነሻ ጽሁፋቸውም፥ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር ብትሆንም ተረጅነትና ልመናን ለማስቀረት የነበረው የታሪክ ስብራት የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሳይችል እንደቆየ አስረድተዋል።

የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በአስር ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር 490 ወረዳዎች ላይ የሚተገበር ሲሆን በፕሮግራሙ 859 ሺህ 685 አባውራዎች/እማወራዎችን በአጠቃላይ 4.2 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ከተረጅነት ወደ ትርፍ አምራችነት የቀየረ ፕሮግራም ነው፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች እና የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

