FDRE Ministry of Agriculture

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ከማሳደግ ባሻገር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም 6ኛው የጋራ ግምገማ እና የትግበራ ድጋፍ ተልዕኮ የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡

ከዓለም ባንክ እና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ 6ኛው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የጋራ ግምገማ እና የትግበራ ድጋፍ ተልዕኮ ከመስከረም 4 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከሁለት ቀናት ውይይት በኃላ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በፕሮግራሙ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ ይደረጋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ይልማ ሲሳይ ፕሮግራሙ የግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳችንን ለማፋጠን ከተቀረፁ በጣም አስፈላጊ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙ ምርታማነትን ከማሳደግ በላይ የሚሻገር መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፣ የገበያ ትስስርን የማጠናከር፣ የአርሶ አደሩን ገቢና ኑሮ የማሻሻል፣ የገጠር ስራ እድልን የመፍጠር እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓትን የማሻሻል ትልቅ አላማ ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ ይልማ አክለውም ፕሮግራሙ ለአርሶ አደሮች እንዲሁም ለማህበረሰቡ የሚጨበጥ ውጤት እንዲያመጣ ከሁሉም አጋሮች ጋር በቅርበት ለመስራት ሙሉ ቁርጠኝነት አለው ብለዋል።

የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ከበሩ በላይነህ በበኩላቸው፣ ላለፉት 3 ዓመታት በስኬት ሲተገበር የቆየው ይህ ፕሮግራም የመካከለኛ ዘመን ግምገማውን ማጠናቀቁንና አሁን ላይ ወደ 4ኛ ዓመት የትግበራ መርሃ-ግብር በይፋ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

ይህ 6ኛው የጋራ ግምገማ እና የትግበራ ድጋፍ ምልከታ በፕሮግራሙ የእድገት ጉዞ ውስጥ ወሳኝ የሽግግር ወቅት በመሆኑ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ቦታ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ከበሩ፣ ውጤታማ የክትትል እና ግምገማ ስራ የልማት አጋሮቻችንን፣ አስፈጻሚ አካላትን እና ዋና ዋና ባለድርሻ አካላትን በጋራ ራዕይ ስር የሚያስተሳስር የተቀናጀ እና ከፍተኛ ትብብርን የሚጠይቅ ጥረት ነው ብለዋል።

ለሚቀጥሉት 11 ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የመስክ ምልከታ በ3 ዋና ዋና ምዕራፎች ተከፍሎ የሚካሄድ መሆኑን የገለፁት ብሔራዊ አስተባባሪው የቴክኒክ እና የሰነዶች ግምገማ፣ መስክ ምልከታ እንዲሁም የከፍተኛ አመራሮች ማጠቃለያ የቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እና የጋራ ስምምነት ሰነድ ማዘጋጀት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የምግብ ስርዓትን የማሻሻልና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አቅምን የመጨመር ዓላማን ያነገበ ሲሆን በአስር ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በ183 ወረዳዎች ውስጥ በ4,301 ቀበሌዎች ላይ የተቀናጀ አሰራርን በመከተል የሀገራችንን የምግብ ስርዓት ዘላቂ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ሲሆን በሀገርአቀፍ ደረጃ 4.1 ሚሊዮን አባ/እማ ወራዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡