ቢሾፍቱ፣ ነሐሴ 28/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የ2018 ዓ.ም የፕሮጀክቱ አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ 4ኛው የአብይ ኮሚቴ ስብሰባ ተካሂዷል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ እንደተናገሩት፣ ፕሮግራሙ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት አሁን ላይ የተከናወኑ ተግባራት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በጥብቅ መመልከት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በፕሮጀክት አፈፃፀም ረገድ አበረታች እና ጥሩ የሚባሉ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በቀጣይም የዜጎችን ህይወት በቀጥታ መለወጥ የሚያስችሉ እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገሩ ዘላቂ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ብሄራዊ አስተባባሪ አቶ ከበሩ በላይነህ የፕሮግራሙን የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ አቅርበዋል።
ፕሮግራሙ በሁሉም የግብርናው ዘርፍ በርካታ የልማት ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰው፣ በ2019 በጀት ዓመትም እነዚህን የልማት ስራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል በዕቅድ መያዙን አቶ ከበሩ በላይነህ ባቀረቡት ፅሁፍ አብራርተዋል።
በመድረኩም በቀረቡት የፕሮጀክቱ የ2018 እቅድ አፈፃጸም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የ2019 ዓ.ም የፕሮጀክቱ በጀት ፀድቋል።
የግብርና ሚኒስቴር፣ የተጠሪ ተቋማት፣ የክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊዎችና የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተሳትፈዋል።
