FDRE Ministry of Agriculture

የምግብ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ!

ቢሾፍቱ፣ ነሐሴ 21/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ባለፈ በዋና መ/ቤቱ የሰራዊቱን የምግብ ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን ሰፊ የተቀናጀ ግብርና ልማት ሥራዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ክበቦችና መደብሮች መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ንጉሴ ለማ እንደገለጹት፣ ተቋሙ በ2018 ዓ.ም በ3,400 ካሬ ሜትር ስፋት ተገንብቶ በ30,000 ጭጩት አሳ የጀመረው ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ አሁን ላይ ቁጥሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

በቀጣይም ወደ 5,700 ሄክታር በማስፋት ትልቅ የአሳ ማከፋፈያ ማዕከል ለመሆን አቅዶ እየሠራ ሲሆን፣ ይህ ራዕይ እውን እንዲሆንም ከግብርና ሚኒስቴርና ከምርምር ተቋማት ተጨማሪ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አዝዝ አያሌው ተቋሙ በወተት፣ በዶሮ፣ በንብና በእንስሳት ማድለቢያ ልማት የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን በማከናወን የራሱን ፍላጎት በማሟላት ለሌሎች የመንግሥት ተቋማት አርአያ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ምንም ዓይነት ልማት ያልነበረበት ጫካ የነበረው ቦታ ወደ ምርታማ የስንዴ፣ የቡናና የአሳ ልማት ቦታ መቀየሩን አድንቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህ ድጋፍ ተቋሙ ራሱን ችሎ ከማምረት አልፎ የምግብ ዋስትናን ለማረጋጥ የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያስችለዋል ብለውዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የአሳ ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን፣ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችንና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በማቅረብ ለተቋሙ የሚያደርገውን ድጋፍ የበለጠ ለማስፋት ማቀዱን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ጌዲዮን ነጋሸ

ፎቶ፡- ዮዲት እንዳለው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *