ግብርና ሚኒስቴር የግብርናውን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠን እና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከቀረፃቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የሆነው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) በርካታ ዜጎችን ወደ አምራችነት በማሸጋገር ከድህነት አላቋቸዋል፡፡
ፕሮግራሙ በስራ አጥነት በቤተሰብ ላይ ጥገኛ ሆነው የሚኖሩና በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው አምራች እንዲሆኑ ካደረጋቸው ውስጥ የጓሪየ የገብስ ዘር አምራች ኢነተርፕራይዝ እና የጉግላ የስንዴ ምርጥ ዘር አባዥ ማህበር አባላት ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

ጓሪየ የገብስ ዘር አምራች ኢነተርፕራይዝ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከልል ጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በጆንቦሮ ቀበሌ 27 (11 ሴቶችና 16 ወንዶች) ስራ-አጥ ወጣቶች ተደራጅተው ያቋቋሙት ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
ወጣቶቹ በህዝብ ንቅናቄ የጠረጴዛ እርከን ተሰርቶለት ያገገመ 10.5 ሄክታር መሬት ላይ ተደራጅተው ያለሙ ሲሆን ማሳ ላይ ያለው የገብስ ምርጥ ዘር ተመልካቹን ከማርካቱ ባሻገር የነገውንም ተስፋ አመላካች ነው፡፡
ወጣቶቹ የተሰጣቸው መሬት በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ በመሆኑ ፕሮግራሙ ባደረገላቸው 75 በመቶ ድጋፍ በ200 ከረጢት ኖራ በማከም በቂ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያን በመጠቀም በአግባቡ ማልማት ችለዋል፡፡
በማሳው ላይ በተደረገው ጥናት መሰረት ከዚህ ከመጀመሪያው ምርታቸው 370 ኩንታል የገብስ ምርጥ ዘር ምርት እንደሚገኝ አቶ አንድአምላክ ንማኒ የጉመር ወረዳ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ ጠቅሰዋል፡፡
ምርቱ ሲሰበሰብ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት የሚቀርብ ሲሆን ወጣቶቹ ያለሙት መስራች ዘር ዋጋው ውድ በመሆኑ ጥሩ ገቢ ያገኛሉ፡፡
ወጣቶቹ በፕሮግራሙ ሁለገብ (በበጀት፣ በስልጠና፣ በክትትልና ሙያዊ ምክር) ድጋፍ ከጥገኝነት ኑሮ እና ከአልባሌ ቦታ ውሎ ተላቀው በአምራችነት ለዚህ ውጤት በመድረሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፣ ለላቀ ውጤም ጠንክረን በመስራት ከራሳችን አልፈን ለሀገራችን ብልፅግና የድረሻችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት በጊዜው ባለው ዋጋ ላይ 15 በመቶ ጨምሮ ስለሚገዛቸው ወጣቶቹ ከዘንድሮ ምርታቸው ከ3.3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡

ሌላው በስልጤ ዞን ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በደረውት ሠመረዲን ቀበሌ የሚገኘው ጉግላ የስንዴ ምርጥ ዘር አባዥ ማህበር ነው፡፡
ማህበሩ ከተቋቋመ 2 ዓመቱ ሲሆን አባላቱ ወንድ 14፣ ሴት 14 በድምሩ 28 አባላት አሉት፡፡ የማህበሩ አባላት በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ በ8 ሄክታር መሬት ላይ አምና ካለሙት የስንዴ ምርጥ ዘር 340 ኩንታል አምርተዋል፡፡
በፊት በስራ አጥነት ሲቸገሩ የነበሩ የማህበሩ አባላት ከጥገኝነት ወደ አምራችነት ተሸጋግረው ያመረቱትን ምርጥ ዘር ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት በማቅረብ ወደ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡
በምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፐሮግራም አስተባባሪ አቶ ጀማል ናስር በፊት እንደ ክልል የስንዴ ምርጥ ዘር እጥረት እንደነበር ጠቅሰው፣ ዛሬ የወረዳውን አርሶአደሮች የስንዴ ምርጥ ዘር በአካባቢው በጥሩ ዋጋ ማግኘት ከማስቻሉም ባሻገር ለሌሎች አካባቢዎችም ማቅረብ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

አሁን አምራቾች ሆነን ተስፋችን ለምልሟል ያሉት ያማህበሩ አባላት፣ ወደፊት ስራውን አስፍተው ወደ ኢንቨስተርነት ለመቀየር ሀሳብ እንዳላቸው ጠቁመው ለዚህ ውጤት እንዲበቁ የደገፋቸውን የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራምን አመስግነዋል፡፡
አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው
