FDRE Ministry of Agriculture

የመኖ ባንክ ልማት የድርቅ ጊዜ አደጋን ለመቋቋም!

በአፋር ክልል የእንስሳት ሀብት ምርታማነትን ለማሳደግና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ‎የእንስሳት ልማትን የሚወስኑ 3 ቁልፍ ጉዳዮች፡- መኖ ልማት፣ ዝርያ ማሻሻል እና ጤና አገልግሎት ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በክልሉ በ2019 በጀት ዓመት በ31 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ ከ470 ሺህ ቶን በላይ መኖ በማልማት ከ52 ሺህ በላይ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተጥሏል፡፡

በሦስቱ የመኖ ልማት ስትራቴጂዎች፡ በመኖ ባንክ ልማት፣ በተሻሻለ የጓሮ መኖ ልማት እና በወል ግጦሽ መኖ ልማት ላይ በብዛትና በጥራት የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው፡፡

በሰፋፊ መሬቶች ገበያ ተኮር የመኖ ባንክ በመስኖ በማልማትና በማከማቸት ምርቱን ለድርቅ ወቅት የአደጋ ጊዜ ምላሽ እንዲዉል ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በ6 ሺህ 875 ሄ/ር መሬት የመኖ ባንክ በማልማት ደረቅ መኖ ምርት 295 ሺህ 625 ቶን ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡

የወረር የግብርና ምርምር ማዕከል እና በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ድጋፍ የተቋቋመው የድርቅ ማቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም ድጋፍ አድርጓል፡፡

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ከመኖ ዘር አዘራር ጀምሮ በማሽን የማጨድና ማሰር ሂደቶችን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የድርቅ ማቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም በክልሉ በተመረጡ 4 ወረዳዎች (አሚባራ፣ ጭፍራ፣ ዳዌ እና ተላለክ) ከ40 በላይ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ፕሮራሙ ቋሚ ወንዞችን በመጥለፍ፣ ቋሚ የወንዝ ውሃ በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ የከርሰ ምድር ውሃን በማውጣት ለእስሳት መኖ ልማት ከማዋል ባሻገር ለሰዎችና ለእንስሳት መጠጥ እንዲውል አድርጓል፡፡

በአሚባራ ወረዳ ፕሮሶፊስ የተባለውን ‎መጤ ዛፍ በመመንጠር 50 ሄ/ር የመኖ ባንክ በመስኖ ለምቷል፡፡ ከመኖ ባንክ ጎን ለጎን በፀሐይ ሃይል የሚሰራ ፓምፕ በመጠቀም የውሃ አቅርቦትን አሳድጓል፡፡ ይህም አርብቶ አደሮች ውሃና የእንስሳት ግጦሽ ፍለጋ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቀነስ እፎይታ ፈጥሮላቸዋል።

እየለማ ያለው የመኖ ባንክ 100 አባላት ያሉት ሲሆን ከመኖ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የስራ ዕድል የፈጠረላቸው ሲሆን በዝናብ እጥረት ለሚከሰት ችግር ምላሽ ይሰጣል፡፡