ወላይታ ሶዶ፣ ሚያዚያ 30/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) መንግሥት የሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት ንዑስ ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት አድርጓል።

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በአበባ ኢንቨስትመንት ብቻ የተያዘውን 1,750 ሄክታር መሬት በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ወደ 3 ሺህ ሄክታር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ ተናግረዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ ለባለሀብቶች የተዘጋጀውን 100 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች መሠረተ-ልማቶችን በማሟላት ለኢንቨስትመንት ምቹ መደረጉን የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ እታገኘሁ ኃ/ማርያም ተናግረዋል።

ይህ የልማት እንቅስቃሴ ባለሀብቱንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በእኩልነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም ባለፈ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው የሆርቲካልቸር ዘርፍን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች በስፋት እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸው የግሉ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚጫወተውን ሚና ለማጠናከር ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ዋነኛ መሠረት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ጌዲዮን ነጋሸ
ፎቶ፦ ያሬድ አሰፋ
