FDRE Ministry of Agriculture

የሆርቲካልቸር ልማትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

ባቱ፣ ግንቦት 12/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የዞን የስራ ሃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳሜ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ እንዲሁም ባቱ ከተማ ወጣቶች ተደራጅተው በክላስተር ያለሙትን የሙዝ እና ሎሚ ማሳን እንዲሁም የሼር ኢትዮጵያ የአበባ ልማትን ጎብኝተዋል፡፡

የግብርና ሚንስትሩ አዲሱ አረጋ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት መንግሥት ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በእነዚህ ምርቶች የሚሸፈነው መሬትና የምናገኘው የውጭ ምንዛሬ፣ እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት አስር ወራትአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ወደ ውጭ በመላክ ከ408 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት እንደተቻለ አብራርተዋል።

ይህንንም ለማሳደግ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ያነሱት ሚንስትሩ ከክልሎች ጋር በመነጋገር በኦሮሚያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በአማራ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የመሬት ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም አሁን ያለውን የአበባ እርሻ በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠርና ከዚህ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ ላይ የተጀመሩ ስራዎች መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ጊዜ እንደሚሆን ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ወቅት በዘርፉ ከተሰማሩ የአበባ አምራች ኩባንያ ሃላፊዎችና ተወካዩች ጋርም ውይይት ተደርጓል።

ዘጋቢ፦ ሰለምን ደምሰው

ፎቶ፦ ተክለመድህን አቻምየለህ