FDRE Ministry of Agriculture

ዘንድሮ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይለማል

(አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ስነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ይሰራሉ፡፡

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮ ዑደትን ባላማከለ መልኩ በነበረው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ምክንያት በቢሊዮን ቶን የሚገመት ለም የአፈር ሀብታችን እየታጠበ ሲወጣ ቆይቷል።

በዚህም ከ54 ሚሊየን ሄክታር በላይ የሚገመት መሬት ተሸርሽሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መስጠት ከሚችልበት ደረጃም ደርሶ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ።

ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በተሰሩ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን የዘንድሮውን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን አስመልክተው እንዳብራሩት የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የቅድመ-ዝጅት ስራዎች በበቂ ሁኔታ እየተከናወኑ ነው፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ስራ አመቱን ሙሉ የሚሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ፋኖሴ፣ በቅድመ-ዝግጅት ምዕራፍ ወቅትም ግንዛቤን ማስጨበጥ፣ ቀያሽ አርሶ አደሮችን ማሰልጠን፣ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት፣ ተፋሰሶችን የመለየትና የማጠር እንዲሁም ሌሎች የቅድመ-ዝግጅት ስራዎችም በትኩረት እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በየአመቱ እንደየክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ከ30 እስከ 60 ቀናት አርሶአደሮችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በየተፋሰሱ እየወጡ የተለያዩ የስነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ያከናውናሉ፡፡

ዘንድሮ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት ታቅዷል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፍር፡- ያሬድ አሰፋ

#ከማምረትበላይ

#BeyondProduction