FDRE Ministry of Agriculture

ዘመናዊ የሩዝ ልማት በጨራቂ ቀበሌ!

የሩዝ ልማት ከለውጡ ወዲህ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት በፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ መንግስት ሀገራችን ለሩዝ ልማት ያላትን ምቹ ስነ-ምህዳር ከግምት በማስገባት በትኩረት በመስራቱም አበረታች ውጤት ተገኝቷል፡፡

በተለይም ግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የሩዝ ፍላግሽፕ ፕሮግራም ቀርጾ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የሩዝ ምርትና ምርታማነት እድገት እየተፋጠነ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የሩዝ ልማት ስራን ወደ ሁሉም ክልሎች ከማስፋፋት ባሻገር ከኩታ-ገጠም እርሻ አሰራር ጀምሮ ልማቱን በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን በኩታ-ገጠም እየለማ ያለው ሩዝ ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ግብ በቅርብ ጊዜ አውን እንደሚሆን አመላካች ነው፡፡

በሊሙ ኮሳ ውረዳ ጨራቂ ቀበሌ ደግሞ ለሩዝ ልማት እጅግ የታደለ ነው፡፡ ለጥ ያለው ረገረጋማ ሜዳው ለሩዝ ልማት መፈጠሩን በኩታ-ገጠም እየለማ ያለው ሩዝ ይመሰክራል፡፡

ወደ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ ሞዴል አርሶ አደሮች በዚህ በጨራቂ ቀበሌ ሩዝን በኩታ-ገጠም በስፋት እያለሙ ሲሆን ከእነሱ ውስጥ አቶ ፀጋዬ ሰይፉ አንዱ ናቸው፡፡ ከወረዳው ቡሳ ጎኖፋ ጋር አምስት ሆነው 310 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ-ገጠም ሩዝ እያለሙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የአቶ ፀጋዬ ሰይፉ 50 ሄክታር ነው፡፡

አቶ ፀጋዬ በቀበሌው የሩዝ ልማትን ከጀመሩ ዘንድሮ ሶስተኛ ዓመታቸው ሲሆን አምና በሄክታር 30 ኩንታል ማምረት ችለዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ አሁን በማሳ ላይ ከሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በሄክታር ከ40 እስከ 50 ኩንታል የሩዝ ምርት ይጠብቃሉ፡፡

እንደ ጅማ ዞን ደግሞ በኩታ-ገጠም ከተዘራው 294 ሺህ 125 ሄክታር መሬት 12 ሚሊዮን 059 ሺህ 125 ኩንታል የሩዝ ምርት ይጠበቃል፡፡

ሩዝን ከሌሎቹ ሰብሎች ልዩ የሚያደርገው ካልተፈተገ በተባዮችም ሳይደፈር ያለምንም ብልሽት መቆየት መቻሉ ነው ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ በዘመናዊ መጋዘን ያከማቹት የሩዝ ምርታቸውን በማቀነባበር እሴት ጨምረው ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ነግረውናል፡፡

አምራቾች ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ግብን አውን ለማድረግ በቁርጠኝነት ሲሰሩ ሸማቾችም ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ ሰጥተው መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡