ቀደምት አባቶቻችን እና አያቶቻችን በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ነበር ኢትዮጵን ያፀኑት፡፡ አድዋ ዛሬ ላይ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የድል አርማ፣ የአንድነታችን እና የብልፅግናችን ማሳያ ነው። ነገን ዛሬ ላይ ሆነን ለመጭው ትውልድ የምናወርሰው የአንድነት፣ የመተባበር የብሩህ ተስፋ እንዲሁም የፅናት መሠረት ነው አድዋ።
ትናንት በዓድዋ ተራሮች ላይ የተጻፈው ደማቅ ታሪክ የነፃነት አርማችን ሲሆን ወራሪው የፋሺስት ጣሊያን ኃይል በዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ ሲመጣ፣ ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን የታጠቁት ግን አንድነትንና መተባበርን ነበር።
በዚህም የተመዘገበው አኩሪ ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ከመሆኑም ባሻገር እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆምን፣ ከተባበርን፣ በአብሮነት ስሜት ከተጋገዝን የማይቻል ነገር እንደሌለ ለዓለም ያስመሰከርንበት ወርቃማ የድል ታሪካችን ነው።
ይህ የድል ታሪካችን ሕያው ምስክርና መገለጫችን ሲሆን በዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ በልማት ስራዎች ላይ አርበኝነታችንን በመድገም ደማቅ ታሪክ ለመፃፍ በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርበታል፡፡
ዛሬ ላይ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነታችን ለማስጠበቅ እና የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ በለውጡ መንግስት ትልቅ ትኩረት የተቸረው ሲሆን በዚህም የአረንጓዴ አሻራ፣ የመስኖ ስንዴ ልማት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ እና ተግባራዊ በማደረግ በዘርፉ ታሪካዊ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ስንዴን በመስኖ በማልማት በየዓመቱ እስከ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር አውጥታ ከውጭ የሚታስገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ የስንዴ ምርት ከመተካት ባሻገር ዛሬ ላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራች ነው፡፡
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት ከ4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ ስንዴን መስኖ በማልማት ከ175 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ልክ እንደ ዓድዋ መላው ኢትዮጵያውያንን ከህፃን እስከ አዋቂ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በማስተባበር ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተሰራው ተከታታይ ሥራ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17.2 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ይፋ የተደረገው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ዋና ዓላማውም የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሲሆን በዚህም ባለፉት ዓመታት በኢኒሼቲቩ አማካኝነት በእንስሳት ሀብት ዘርፉ ላይ በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

የከተማ ግብርና ልማትም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና የገበያ ዋጋን ከማረጋጋት ባሻገር የግብርና ስራ በገጠር ብቻ ሳይገደብ በከተሞችም በስፋት እንዲተገበር በማድረግ ትልቅ አበርክቶ እያደረገ ነው፡፡

ዓድዋ የትናንት ድላችን፣ የዛሬ ማንነታችን እና የነገ ተስፋችን ከመሆኑም ባለፈ የብልፅግናችን አይቀሬነት ማሳያ ነው፡፡

አንድነታችንን በማፅናትና በማጠናከር በሁሉም የግብርና ልማት መስኮች ላይ ምርታማነታችንን በማሳደግ የተረጂነት ታሪካችን በመቀልበስ ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ለማረጋገጥ መላው የሀገራችን ህዝቦች መረባረብ ይኖርብናል፡፡

አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው