FDRE Ministry of Agriculture

ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳበው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብርና

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የኢትዮጵያ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት በማግኘት ረገድ በአዲስ እና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡

ሀገሪቱ ተግባራዊ ያደረገችው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የተጠናከረ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት ማዕከል አድርጓታል።

በዚህ ሰፊ የእድገት እንቅስቃሴ ውስጥ የግብርናው ዘርፍ በተለይም የንግድ፣ የኤክስፖርት እና የግብርና ምርቶች ማቀናበሪያ ስራዎች፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን እና ባለሃብቶችን ትኩረት በመሳብ የሀገሪቱን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን እያፋጠነ ይገኛል።

ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች የኢትዮጵያን ሰፊ ያልታረሰ ለም መሬት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና ለስራ ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል በማስተዋል በዘርፉ በሰፊው በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል፣ በኢትዮጵያ በፍራፍሬ እና አትክልት ልማት ላይ የተሰማራው የህንድ የኢንቨስትመንት ድርጅት ጉድ አግሮ ባለአክሲዮን ጋጄንድራ ሲንግ ማንፑራ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ፣ ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለኤዥያ ገበያዎች ያላት ስትራቴጂካዊ ቅርበት ለኤክስፖርት ንግድ እጅግ ተመራጭ ያደርጋታል።

ድርጅታቸው በአቮካዶ እና መሰል ምርቶች ላይ ያደረገውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በመቀጠል፣ ያዋለውን 500 ሺህ ዶላር ኢንቨስትመንት በሦስት እጥፍ በማሳደግ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ለማድረስ ማቀዱ የዘርፉን ከፍተኛ እምቅ አቅም ያሳያል።

ከግል ኢንቨስትመንቱ ባሻገር፤ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ግብርና ትግበራ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንቅስቃሴዎች በዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እና ተቋማት ዘንድ ትልቅ አድናቆትን አትርፈዋል፡፡

ለአብነትም የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሲያ በኦሮሚያ ክልል ያደረጉት ጉብኝት የሀገሪቱን ዘመናዊ የግብርና ልማት፣ የላቀ የዘር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የሜካናይዜሽን እርሻ በቅርበት የተመለከቱበት ነበር።

በሻሸመኔ ከታዋቂው የአሜሪካ ግብርና ማሽነሪ አምራች ጆን ዲር አጋሮች ጋር የተደረገው የሥራ ትስስር ለዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት እና ከውጭ ኢንቨስትመንት የሚገኘውን የሀገር ውስጥ የሥራ እድል ፈጠራ አጉልቶ አሳይቷል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንቨስተሮች የሚሰጣቸው የቀረጥ ነጻ ማበረታቻዎች፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እና ተመራጭ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎች የውጭ ካፒታል ፍሰቱን እያጠናከሩት ይገኛሉ።

በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ማዕድን ዘርፎች ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎትም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።

የኢትዮጵያ ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የተፈጥሮ ጸጋውን ከዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር እና ከዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ጋር በማጣመር፣ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ በዓለም አቀፍ የግብርና ንግድ መድረክ ላይ ያላትን ተወዳዳሪነት፣ ተቀባይነት እና የኢኮኖሚ አቅም ከፍ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወት የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘገባ ያስረዳል።