የንብ ሀብት ልማት ምርታማነት የሚወሰነው ካለው የህብረ-ንብ ቁጥር ባለፈ የአየር ሁኔታ፣ የንብ መኖ ተክሎች የሚያብቡበት ጊዜ እና ወቅታዊ የንብ እንክብካቤ ስራዎችን በትክክል በመለየት መተግበር ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህም ንብ አናቢዎች በአካባቢያቸው ያሉ የንብ መኖ ተክሎችን አይነትና የአበባ ጊዜያቸውን በማወቅ ሥራቸውን ከወቅቱ ጋር አጣጥመው መስራት ይገባቸዋል።
በተለይም ከነሐሴ አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ ባለው ጊዜ ለቀጣዩ የማር ምርት ወቅት ጠንካራ መሠረት የሚጣልበት በመሆኑ የንብ መኖ ተክሎችን መትከልና መንከባከብ፣ የንብ ማነቢያ ቦታንና ቀፎዎችን ማጽዳት፣ የተበላሹ ቀፎዎችን መጠገንና የቀፎ ማስቀመጫዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል። የንብ ጤናን መጠበቅ አንዱ ተግባር በመሆኑ በሽታና ተባይ በወቅቱ መከታተል እና በቅንጅታዊ አሰራር የፀረ-ተባይና የፀረ-አረም መድኃኒቶች አጠቃቀም ንቦችን በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የህብረ-ንብ ጥንካሬን ለመጨመር በቂ ምግብ መስጠት፣ የንግሥት ንብ ማባዛትን ማበረታታትና ለቀጣዩ የማር ወቅት ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል። የተፈጥሮ ፖለን ምንጭ (የአበባ ብናኝ) በሚጎድልበት ጊዜ ይህን የሚተካ ተገቢ የሆነ ተጨማሪ ምግብ በመስጠት ህብረ-ንቦችን ለማባዛት፣ ለማዛወርና የማር ምርትን ለማጠናከር ያስችላል።
የግብዓት እና ቴክኖሎጂ አቅርቦትና ስርጭት ለምርታማነት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ የተሻሻሉ የፍሬምና የሽግግር ቀፎዎችን ማዘጋጀት፣ ነባር ቀፎዎችን ማጽዳት፣ ያረጁ የሰም እንጀራዎችን በአዲስ መተካት እና የሰም እንጀራ ማዘጋጀት የወቅቱ ዋነኛ ስራዎች ናቸው። ከባህላዊ ቀፎ ወደ ተሻሻለ ቀፎ የሚዛወሩ ጤናማ ህብረ-ንቦችን በመምረጥ በቂ የማዛወሪያ ቦታና ቁሳቁስ ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባል።

በምርት ወቅት የማር ምርትን በጥራት ለመሰብሰብ እንዲቻል የማር ማውጫ፣ ማጣሪያ፣ ንጹህ ማጠራቀሚያና ማሸጊያ ቁሳቁሶችን አስቀድሞ ማሟላት ያስፈልጋል። ያልደረሰ ማር አለመሰብሰብ፣ የምርት ንጽህናን መጠበቅና ተገቢውን የማር አያያዝ ሂደት መከተል ለምርት ጥራትና ለገበያ ተወዳዳሪነት መሠረታዊ ስራዎች ናቸው።
በንብ ማነብ ሥራ ወቅት የአየር ሁኔታንና የአበባ ጊዜን መከታተል፣ ቀፎ ሲከፈት ተገቢውን የመከላከያ ልብስ፣ ጓንትና የዓይን መከላከያ መጠቀም እና ንቦችን ለማረጋጋት ጥቅም ላይ የሚውለው ጭስ ንቦችን የማይጎዳ መሆኑን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ይህንን ሁሉ ለማሳካት ንብ አናቢዎች ወቅታዊ አጫጭር የመስክ ስልጠናዎችን እና የልምድ ልውውጦችን ማድረግ እንዲሁም ስለ ገበያ ትስስርና የምርት ጥራት ደረጃዎች በቂ ግንዛቤ ማግኘት ይገባቸዋል።

የመረጃ አያያዝን በማጠናከር የህብረ-ንብ ብዛት፣ የቀፎ ሽፋን፣ የበሽታና የተባይ ሁኔታ እንዲሁም የግብዓት አጠቃቀም በየደረጃው በትክክል እየመዘገቡ ለቀጣይ ስራ እንደ ግብዓት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶ፡- ዮዲት እንዳለው
