ያቤሎ፣ ጳጉሜን 2/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የቦረና ዝርያ ከብቶች በውስን የመኖ አቅርቦትና በፈታኝ የአየር ንብረት ውስጥም ሆነው በቂ ሥጋና ወተት በመስጠት፣ እንዲሁም ድርቅንና በሽታዎችን በመቋቋም የሚታወቁ ልዩ የሀገራችን የዘረ-መል ሀብት ጸጋዎች ናቸው።
እነዚህን ጠንካራና ምርጥ ዝርያዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር፣ ለማህበረሰቡ የማሰራጨት ታሪካዊ አደራን ተሸክሞ የሚገኘው የቦረና ዳልጋ ከብት ማራቢያና ማሻሻያ ማዕከል በ1979 ዓ.ም ነበር የተመሰረተው፡፡
ማዕከሉ የተለያዩ ፈተናዎችን፣ ውጣ ውረዶችንና ታሪካዊ አውዶችን በፅናት አሳልፎ ዛሬ ላይ የደረሰ ሲሆን ምርጥ የቦረና ከብት ዝርያዎችን በዘላቂነት በማቆየትና በማሻሻል ረገድ ለሀገሪቱ ያበረከተው ውለታ እጅግ ከፍተኛ ነው።

በ1983 ዓ.ም በነበረው የመንግስት ለውጥ የማዕከሉ እንቅስቃሴ ተቋርጦ የነበር ቢሆንም የቦረና ዝርያዎችን ለማስቀጠል ባለው ቁርጠኝነት በ1985 ዓ.ም በ11 ከብቶች ብቻ ዳግም በማንሰራራት የእርባታ ሥራዎችን ጀመረ።
ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ አቅሙን ደረጃ በደረጃ እያጠናከረ የመጣው ማዕከሉ፣ ለአካባቢው አርብቶ አደሮችና ለተደራጁ ማህበራት የተሻሻሉ የቦረና ዝርያ ከብቶችን በማሰራጨት የሥጋና ወተት አቅርቦትን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ 670 የቦረና ዝርያ ከብቶች ያሉ ሲሆን ይህም በትውልድ ቅብብሎሽ ምርጥ ዝርያዎችን ከማስቀጠል ባሻገር፣ ለአርብቶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብሎም ለሀገራችን የእንስሳት ሀብት ልማት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
