FDRE Ministry of Agriculture

ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን ዕውን የማድረግ ተግባር

(ሐዋሳ፣ ታህሳስ 21 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

የግብርናውን ዘርፍ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የተለያዩ የመስኖ አማራጮችን በመጠቀምና ምርታማነትን በማሳስደግ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል።

ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶአደሮች በየአካባቢው ያሉትን የውሃ አማራጮች በመጠቀም በመስኖ በመታገዝ አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ ይገኛሉ፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በዛሬው ዕለት በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ዙሪያ እና ሸበዲኖ ወረዳዎች ላይ የመስኖ ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በወረዳዎቹ የመስኖ አማራጭን በመጠቀም እየለማ የሚገኝ የቲማቲም፣ ጥቅልጎመን፣ ቃሪያ እና ሌሎች የአትክልት ክላስተሮችን እንዲሁም የቡና ልማትን ተመልክተዋል።

ሚኒስትሩም በዚሁ ወቅት ባለአነስተኛ ይዞታ የመስኖ አምራች አርሶአደሮች ማሳ ላይ በመገኘት አርሶአደሮችን አበረታተዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አርሶአደሮች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኑሮዓቸውን ለመቀየር የጀመሩት ሥራ የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የእርዳታ እህል ይሰፈርላቸው የነበሩ አርሶአደሮች በአነስተኛ ይዞታ ማሳቸው ላይ በአትክልት ልማት ተሰማርተው በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ ሲሉም ተናግረዋል።

አርሶአደሮች መስኖን በመጠቀም የሚያለሙት የተለያዩ የአትክልት ምርቶች ከክልሉ ፍጆታ ባለፈ ለማዕከላዊ ገበያ በመላክ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽዖ ከማበርከቱም ባሻገር የአምራች አርሶአደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው።

በሲዳማ ክልል በአንደኛ ዙር የመስኖ ልማት 80 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ አትክልቶች የለማ ሲሆን 18 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

በሃገር አቀፍ ደረጃ በአንደኛ ዙር የመስኖ ልማት በዋና ዋና የአትክልትና ስራስር ሰብሎች እስካሁን ከ806 ሺህ 184 ሄክታር በላይ የለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ከ135 ሺህ 563 ሄክታር በላይ የሚሆነው በክላስተር ለምቷል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፈር፦ ተክለመድህን አቻምየለህ