FDRE Ministry of Agriculture

ከውጭ የሚገባውን የሱፍ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት!

ጅማ፣ መስከረም 14/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር፣ የምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት (RTI) ፕሮጀክት ድጋፍ እና በሳማኑ (SAMANU) የዘይት አምራች ካምፓኒ ትብብር በሳማኑና በግብርና ዘርፍ ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል በተደረገው የኮንትራት እርሻ ውል (የአምራች እና አስመራች ውል) መሰረት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በሶኮሮ ወረዳ በባለሀብቶች እየለሙ የሚገኙ የሱፍ ልማት ማሳዎች ተጎብኝተዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል የመጡ አመራሮች እንዲሁም ከጅማ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ አርሶ አደሮች በተገኙበት የመስክ ምልከታው የተካሄደ ሲሆን በዚህም ለአርሶ አደሮች ስለ ሱፍ ልማት በማስተዋወቅ በስፋት በዘርፉ ተሰማርተው እንዲያለሙ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ (ዶ/ር) መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት 9 ሺህ ባለሀብቶች በሰብል ልማት ዘርፍ ተሰማርተው 2.3 ሚሊዮን ሄ/ር መሬት እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮንትራት እርሻ ውል መኖር አምራችና አስመራቹን ተጠቃሚ በማድረግ በምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ ጉልህ አስተዋጾ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።

አሁን ላይ በሱፍ ልማት ላይ በቅንጅት እየተሰራ ያለው ስራ ከውጭ የሚገባውን የዘይት ማምረቻ ጥሬ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት ድርሻው የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል።

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የሶኮሩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አብዱራዛቅ አባጀበል በበኩላቸው በሶኮሩ ወረዳ በአርሶ አደሩ ዘንድ የሱፍ ምርትን የማምረት ፈላጎት እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ በወረዳው በጊቤ አከባቢ በአርሶ አደሩና ባለሀብቶች ከ200 ሄ/ር በላይ መሬት እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከሳማኑ ዘይት አምራች ፋብሪካ ጋር እየተደረገ ያለው የኮንትራት ውል አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር ከድርጅቱ እንዲያገኝ ይረደዋል ያሉት ኃላፊው፣ ይህም አርሶ አደሩ በሙሉ አቅሙ ወደ ሱፍ ልማት እንዲገባ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በመስክ ምልከታው በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በሶኮሩ ወረዳ ቦዴ ቀበሌ በሳማኑና በ8 ባለሃብቶች መካከል በተደረገ የኮንትራት ውል ስምምነት መሰረት እየለማ የሚገኝ ከ90 ሄ/ር በለይ የሱፍ ኩታ-ገጠም ልማት ተጎብኝቷል።