FDRE Ministry of Agriculture

ከእርዳታ ጥገኝነት ወደ አምራችነት፤ የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ምዕራፍ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) ኢትዮጵያ ለዘመናት በምግብ እርዳታና ከውጭ ከሚገባ ስንዴ ጋር ተያይዞ ሲነሳ የነበረውን የታሪክ ገጽ በማጠፍ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የሚያስችላትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍታለች።

ቀደም ሲል ከባህር ማዶ የሚመጣ እርዳታ ጠባቂ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በፖሊሲ ማሻሻያዎችና በተቀናጀ የብልጽግና ጉዞ የሀገር ውስጥ ፍላጎቷን አሟልታ ለጎረቤት ሀገራት መትረፍ ችላለች።

ይህም የህዝቡን የትጋት ባህልና የመንግሥትን የጠራ እይታ አስተሳስሮ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ አዲስ የልማት ምዕራፍ የከፈተ ተግባር ሆኗል።

የዚህ ታላቅ ስኬት መነሻ የመንግሥት ቁርጠኝነትና ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው።

በዚህም ያለውን የመሬት፣ የውሃና የሰው ኃይል ሀብት ተቀናጅቶ ጥቅም ላይ እንዲውል በተደረገው ጥረት ቀድሞ ለልማት የማይታሰቡ እንደ ሶማሌና አፋር ያሉ ቆላማ አካባቢዎች ዛሬ የስንዴ ልማት ማዕከል ለመሆን በቅተዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ በተደረገው ሰፊ እንቅስቃሴም በሚሊየን የሚቆጠር ሄክታር በላይ መሬት በማልማት አርሶ አደሩን በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ተከናውኗል።

ይህ ርምጃ አርሶ አደሩ ዝናብን ብቻ የመጠበቅ ልማዱን ቀይሮ በዓመት ከሶስት ጊዜ በላይ እንዲያመርትና መስኖን የዘወትር ባህሉ እንዲያደርግ አስችሎታል።

ይህ በሀገር ውስጥ የተመዘገበው ስኬት በዓለም አቀፍ መድረኮችም የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ቁመና ከፍ አድርጎታል።

በቅርቡ በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ራሷን በስንዴ ምርት መቻሏን ገልጸዋል፡፡

የስንዴ ምርት እድገት ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚመሰክሩት ቀደም ሲል በዓመት ከ50 ሚሊየን ኩንታል በላይ የማምረት ታሪክ ያልነበራት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ምርታማነቷን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ በዓመት ከ317 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማድረስ ችላለች።

ይህም ቀደም ሲል በአፍሪካ ቀዳሚ የነበረችውን ግብጽ በሶስት እጥፍ በመብለጥ ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉር ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር አድርጓታል።

ይህ የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ ከተመጽዋችነትና ከእርዳታ ጠባቂነት ተላቅቃ የራሷን ዕድል በራሷ እጅ መጻፍ እንደምትችል ለዓለም ያሳየችበት ማረጋገጫ ነው።

የስንዴ ኤክስፖርት ማካሄድ መጀመሩም የመጨረሻው ግብ ሳይሆን ወደላቀ የኢኮኖሚ ከፍታ ለመሸጋገር የተወሰደ የመጀመሪያው ጠንካራ ርምጃ ነው።

በቆራጥነት በዕቅድና በጠንካራ አመራር የተጀመረውን የስንዴ ልማት ሥራ በማስቀጠል የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና የሀገርን ክብር ማስጠበቅ የሚያስችል እውነታ መሆኑን ኢትዮጵያ እየሄደችበት የምትገኘው የልማት ጉዞ በተግባር አረጋግጧል ሲል የዘገበው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው።