በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ከብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ጋር በመቀናጀት ፕሮግራሙ ከሚተገበርባቸው ከ10 ክልሎች ለተውጣጡ 26 ወንድ እና 8 ሴቶች በድምሩ ለ34 የፕሮግራሙ አስተባባሪዎችና ከፍተኛ የፍራፍሬ ልማት ባለሙያዎች በመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ለተከታታይ 4 ቀናት በአቮካዶ እሴት ሰንሰለት ላይ በንድፈ-ሀሳብና በተግባር የተደገፈ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብደላ ነጋሽ እንደተናገሩት ይህ ስልጠና በአጠቃላይ በአቮካዶ የእሴት ሰንሰለት (Value Chain) ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የተዘጋጀ ስልጠና ነው።

በዋናነት ስልጠናው ለክልል የዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጥ ሲሆን ክልሎች ያሉባቸውን ክፍተቶች በመለየት እንዲሁም ያላቸውን አቅም ለመገንባት ትኩረት ያደረጉ ስልጠናዎች በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የተሳተፉ ከፍተኛ የፍራፍሬ ልማት ባለሙያዎች በበኩላቸው ብዙ ጊዜ ግብርና ሚኒስቴር በተግባርም በንድፈ-ሀሳብም የታገዘ ውጤታማ ስልጠናዎች እየሰጠ መሆኑን ተናግረው፣ የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው አንድ ሰብልን መሰረት ያደረገ ስልጠና መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከሰልጣኞቹ መካከል የአማራ ክልል የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ይበልጣል ወንድምነው በአቮካዶ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ ችግኝ ጣቢያዎች ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን፣ እንዲሁም የተከላ የሰብል ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎችና ሌሎች ቴክኒካል ስራዎችን ያካተተ የባለሙያን የአቅም ክፍተት የሚሞላ ስልጠና እንደነበር ተናግረዋል።

የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም እንደ ሀገር የተቀመጠውን ግብ በኤክስፖርትም በምግብ ዋስትናም ረገድ ውጤታማ ለማድረግ ምን ዓይነት ስራዎችን መስራት አለብን የሚለውን በአግባቡ በመሰልጠን ዕውቀት የቀሰምንበት የስልጠና ጊዜ እንደነበር አቶ ይበልጣል ጠቁመዋል።
ሌላኛዋ የስልጠናው ተካፋይ ከሲዳማ ክልል ከፍተኛ የፍራፍሬ ልማት ባለሙያ ሐና ኃ/መስቀል እንደ ሲዳማ ክልል በአቮካዶ ልማት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በተለይም የድህረ-ምርት ብክነትን እንዴት መቀነስ እንችላለን የሚለውን በተግባርም በንድፈ-ሀሳብም ስልጠና የወሰድንበት ነው ብለዋል።
የወሰዱትን ስልጠና ወደ ታች ላሉ የወረዳ እና የቀበሌ ባለሙያዎች በመስጠት፣ እነሱ ደግሞ ለተመረጡ አቮካዶ ለሚያመርቱ አርሶአደሮች ስልጠናውን በማውረድ ሂደት ድርሻቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ አብራርተዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አንጻር መጀመሪያ የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚቀድም የጠቀሰሱት ባለሙያዋ፣ የአቅም ግንባታ ስራው እስከ ታችኛው መዋቅር እስከ አርሶ አደሩ ድረስ ተደራሽ የሚሆንበት አግባብ መፍጠር ከቻልን የሚፈልገውን ምርትና ምርታማነትን አንድ ደረጃ ማሳደግ እንችላለን ብለዋል።

አቶ ሙስጠፋ አማን ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የፍራፍሬ ልማት ባለሙያ ሲሆን ዘመናዊ የአቮካዶ እርሻ በተለይም ደግሞ የክላስተር እርሻ ምን መምሰል እንዳለበት ትልቅ ግንዛቤ ያገኙበት ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከስልጠናው የቀሰምነውን እውቀትና ክህሎት መሰረት በማድረግ በቀጣይ አርሶአደሩ ዘመናዊ የአቮካዶ እርሻን እና የክላስተር የአመራረት ዘዴን እንዲከተል ለማድረግ እንጥራለን ብለዋል።

በመልካሳ ግብርና ምርምር የዕፅዋት ተባይ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሮ ሙላቷ ወንድሙ በበኩላቸው በአቮካዶ ተባዮች ዙሪያ በተለይም የአቮካዶ ተባዮችን መለየት፣ የሕይወት ዑደታቸውንና የመከላከያ ዘዴዎችን የተመለከተ በንድፈ-ሀሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኞች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደየመጡበት ተመልሰው በስራቸው ላሉ ሰዎች እንዲሁም ለአምራቹ አርሶአደር ተደራሽ እንዲያደርጉና የአቮካዶ ምርታና ምርታማነትን ለማሳደግ የበኩላቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ዮዲት እንዳለው
