የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት ቀጣይነትን ለማረጋገጥና አለምአቀፍ የአየር ንብርት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የተፈጥሮ ሀብታችንን ማልማት፣ መንከባከብና በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡
ባለፉት አመታት ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጋር ተያይዞ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በሆርቲካልቸር ዘርፍ ፍሬያማ ውጤት እየታየ ነው፡፡
በዚህም ሀገራችን ለሆርቲካልቸር ልማት ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ተቀርጾ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
አቮካዶ በሀገር ውስጥ ለምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና በውጭ ገበያ ካለው ከፍተኛ ተፈላጊነት አንጻር ልዪ ትኩረት ተሰጥቶት እየለማ ይገኛል፡፡
የአቮካዶ ልማትን ይበልጥ ለማስፋፋት የ15 ዓመት የአቮካዶ ልማት ሀገራዊ ፕሮግራም ተቀርጾ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘት በሚያስችል ደረጃ ላይ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
አነስተኛ ይዞታ ካለው አርሶ አደር እስከ ሰፋፊ የእርሻ መሬት የያዙ ባለሀብቶች አቮካዶን በማልማት ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩና ለፋብሪካዎች ጥሬ ምርት በማቅረብ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በአቮካዶ ልማት ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ወረቁ በዳዳና በተመሳሳይ በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ በአቮካዶ ልማት ተሰማርተው የሚገኙ አርሶ አደር ውዴ ጉዬ ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ሸራ ዲባንዲባ ቀበሌ በአቮካዶ ልማት ተሰማርተው እምርታዊ ለውጥ እያስመዘገቡ የሚገኙት አርሶ አደር ወርቁ አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በ2011 ዓ.ም ይዞላቸው የመጣውን መልካም እድል በመጠቀም ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡
አቮካዶን በስፋት በማልማት በአመት ሁለት ጊዜ ጥራት ያለው የአቮካዶ ምርት ወደ አራት ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለሀገር እያስገኙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለ500 ዜጎችም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
በተመሳሳይ በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ አጃዋ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ውዴ ጉዬ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ከ10 እስከ 15 የተሻሻሉ የአቮካዶ ችግኞችን በጓሯቸውና በእርሻ ማሳቸው በመትከል የአረንጓዴ አሻራው ተሳታፊ ናቸው።
አርሶ አደር ውዴ ባለፉት ግዜያት በትጋት ከተከሏቸው የአቮካዶ ችግኞች ዛሬ ጥሩ ገቢ ማግኘት ችለዋል። በዚህም በየዓመቱ እስከ 100 ኩንታል የአቮካዶ ምርት በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሚገኘው የአቮካዶ ዘይት ፋብሪካ በማቅረብ እና ቀሪውን ገበያ ወስደው በመሸጥ ጥሩ ገቢ ያገኛሉ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከችግኝ ተከላ የአከባቢውን ስነ-ምህዳር አስጠብቋል፤ ለአርሶ አደሮች ዘላቂ ገቢ አስገኝቷል፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተደማሪ አቅም ፈጥሯል፡፡ እንዲሁም በሆርቲካልቸር ምርት የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅዖም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል፡፡
