FDRE Ministry of Agriculture

ከተረጂነት ወደ አምራችነት የሚደረግ ጥረት በአፋር

በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አውሲ ረሱ ዞን የጭፍራ ወረዳ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መደገፍ ከጀመረ አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በወረዳው 25,119 ተጠቃሚዎች  የሚገኙ ሲሆን  በገሪሮ ቀበሌ ብቻ 561 ወንዶች እና 435 ሴቶች አጠቃላይ 996 ተጠቃሚዎች በፕሮግራሙ ታቅፈው የሚደገፉ ናቸው፡፡

ከተቀመጡት የመንግስት አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ በሆነው እራስን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር በምግብ እራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የፕሮግራሙ  ተጠቃሚዎች የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በፕሮግራሙ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች አካባቢውን ወደ ለምነት በመቀየር ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ቦታዎችን በማስፋቱ  የአፋር አርብቶ አደር ቤተሰቡን እና  እንስሳቱን ይዞ ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወር ያገጥሙት የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ እንዲሁም ህብረተሰቡ  በአንድ አካባቢ ተሰባስቦ እንዲኖርና ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን  በማድረግ ረገድ የፕሮግራሙ  ሚና የጎላ ነው፡፡ 

ወ/ሮ መኪያ አህመድበጭፍራ ወረዳ በገሪሮ ቀበሌ የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ ሲሆኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  አላማው በተፈጥሮ ሃብቱ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ነው ብለዋል፡፡ 

ባለሙያዋ አክለውም ፕሮግራሙ ከሚያደርገው ድጋፍ ውስጥ የአቅም ግንባታ መስጠት፣ ግብአት ማቅረብ፣ የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግ እና የእንስሳት መኖ በማቅረብ ህብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ ለተጠቃሚዎች  በዓይነት ወይም በገንዘብ የሚከፍል ሲሆን ተጠቃሚዎች ውሃን በመያዝ የእርሻ ስራን በስፋት  ለመስራት የሚያደርጉትን  ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም  ገልጸዋል፡፡

የጭፍራ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መሃመድ ዶጋ መሃመድ እንደገለጹት በወረዳው ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች ላይ በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር መሸርሸርን በማስቆም በወረዳው የግብርና ምርት ጭማሪ እንዲኖር ከማድረጉም ባሻገር የጭፍራ ከተማ የከርሰ-ምድር ውሃ መጠንም ጨምሯል፡፡

በፕሮግራሙ የሚደገፉ  የቀጥታ ተረጂዎችንም ሆነ ሰርተው የሚከፈላቸው ተጠቃሚዎችን አጠቃላይ መረጃ በመለየት የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም/MIS/ ቴክኖሎጂን በመጠቀም  ከዚህ በፊት ሲያጋጥም የነበረውን የተጠቃሚዎች ዝርዝር ልየታ ችግርንና የተጠቃሚዎች ቅሬታን መቅረፍ እንደተቻለም በጭፍራ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት እና የማኔጀመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ከፍተኛ ባለሙያ  አቶ መሃመድ ጀማል ገልፀዋል፡፡

አቶ ዊቲካ አርባ በገሪሮ ቀበሌ አርብቶ እና ከፊል አርሶ አደር ናቸው፡፡  በፕሮግራሙ ከታቀፉ አመታት መቆጠራቸውን ገልጸው በተሰሩት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ካባቢውን፣ ቤቶቻችንን እና እንስሳትን ይጎዳ የነበረው ጎርፍ  ቆሞ አካባቢው በመልማቱ እኛም ተረጋግተን እየኖርን ነው ብለዋል፡፡

ወ/ሮ አስያ ኮሌይታ በገሪሮ ቀበሌ  አርሶና አርብቶ አደር ናቸው፡፡ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  በቀበሌው ከተጀመረ ወዲህ በጎርፍ ተጠርጎ የሚሄደውን አፈር መከላከል በመቻላቸው  በወንዞችና በተፋሰስ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ቦሮቦሮችም መቀነሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከመምጣቱ በፊት ምንም  ያልነበራቸውና እንስሳትን በመከተል ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ እንደሚኖሩ የገለጹት ወ/ሮ አስያ፣ አሁን ላይ በተፈጠረው እድል  ቤት በመስራትና አንድ ቦታ ላይ በቋሚነት በመኖር ልጆቻቸቸው የትምርት እድል እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው በተመረጡና የእርከን ስራቸው በተጠናቀቁ  ሁሉም ቦታዎች ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በተሰሩባቸው ቦታዎች ጠፍተው የነበሩ እንስሳትና እጽዋትም  ተመልሰዋል፡፡ አካባቢውን አረንጓዴ ከማድረግ ጋር ተያይዞ  የአየር ንብረት ለውጥም ተመዝግቧል፡፡

ፕሮግራሙ የተጠቃሚዎችን  አጠቃላይ የስራ ባህል የቀየረ ሲሆን ተጠቃሚዎቹ የተፈጠረላቸው ምቹ አጋጣጣሚን በመጠቀም የሚፈልጉትን ስራ በመስራት ሀብት እያፈሩ ይገኛሉ፡፡