ሀዋሳ፣ ግንቦት 6/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር የሲዳማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችን ያሳተፈ የፓናል ውይይት መድረክን “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት!” በሚል መሪ ቃል አካሂዷል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቴ አለነ መድረኩን ሲከፍቱ ኢትዮጵያ ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ የነደፈችው ስልታዊ ሽግግር ዛሬ ላይ ተጨባጭ ፍሬ እያፈራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዜጎችን ወደ አምራችነት በማሸጋገር ልመናን ማስቀረት የብሔራዊ ክብራችን መገለጫ ነው ያሉት አቶ እውነቴ ለዚህም የመንግስት፣ የአጋር አካላት እና የሚዲያ ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ ከተቋማት ጋር በመተባበር መሰል መድረኮች እየተዘጋጁ ሀገራዊ ትርክት ዙሪያ ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ከተቋማት ጋር በትብብር መስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

ሀገራዊ ብልጽግናን ከማረጋገጥ አኳያ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከሀገራዊ ርዕይ አንጻር እያበረከተ ያለው አስተዋፅዖ በሰነዱ የቀረበ ሲሆን ድንበር፣ ሕዝብ፣ መንግስት እና ሉዓላዊነት የሀገር መሰሶዎች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግብርና ሚኒስቴር የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምን ተጠቅሞ የዜጎችን ምርታማነት ለማሳደግ ያለው ቁርጠኝነትና የፖሊሲ ማዕቀፍ ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የየክልሎቹ ተወካዮችም በየክልላቸው ያሉ ጸጋዎችን በማልማት ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመቀየር በተጨባጭ የተሰሩ ስራዎችን ካብራሩ በኋላ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረቡት ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፤ ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውንም አካፍለዋል፡፡
በመጨረሻም በየደረጃው ካለው አመራር፣ ከሴክተር መ/ቤቶች፣ ከአጋር አካላት፣ ከሚዲያና ከህዝብ ምን እንደሚጠበቅ ቀጣይ አቅጣጫን በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

የመጀመሪያው የፓናል ውይይቱ መድረክ በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ቀጣዩ መድረክ ደግሞ በድሬደዋ ከተማ ይካሄዳል፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
ፎቶ፡- ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
