በድርቅ ጊዜ የሚፈጠረው የመኖ እጥረት ለእንስሳት ሞት፣ ለምርታማነት መቀነስና ለአርብቶ አደር ኑሮ መዛባት ዋና ምክንያት ይሆናል። ስለሆነም የመኖ ደህንነትን ከድርቅ በፊት ማረጋገጥና በቂ የመኖ ክምችት መፍጠር የእንስሳት ሀብትንና የአርብቶ አደር ኑሮን ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።
የመኖ ማከማቻ መጋዘን (Fodder Bank/Hay Store) በዝናብ ወቅት የሚገኘውን ትርፍ መኖና በመስኖ የለማን መኖ በማሰባሰብ በትክክል በማድረቅና በመጠበቅ በደረቅ ወቅት፣ በድርቅና በአስቸኳይ ጊዜ ለእንስሳት እንዲውል የሚያስችል የመኖ ደህንነት ስርዓት ነው። የመኖ ማከማቻ ማዕከል ብቻውን ሕንፃ ሳይሆን የመኖ ምርት፣ ማሰባሰብ፣ ማድረቅ፣ ማከማቸት፣ ማሰራጨትና አስተዳደርን የሚያካትት ሙሉ ስርዓት ነው።

የመኖ ማከማቻ ማዕከላት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች አሏቸው። የእንስሳት ሞትን ይቀንሳሉ፤ በድርቅ ጊዜ እንስሳትን በዝቅተኛ ዋጋ ከመሸጥ ይታደጋሉ፤ የወተትና ስጋ ምርት እንዳይቀንስ ያግዛሉ፤ የመኖ ዋጋ መዋዠቅን ይቀንሳሉ። በተጨማሪም ለማህበራት፣ ለወጣቶችና ለሴቶች በመኖ ምርት፣ ማሰር፣ ማጓጓዝና ሽያጭ አዲስ የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
ከማህበራዊ አንጻርም የመኖ ማከማቻ ማዕከላት የአርብቶ አደር የኑሮ ዋስትናን ያጠናክራሉ፤ በድርቅ ወቅት የቤተሰብ ምግብ ዋስትናን ለመጠበቅ ያግዛሉ፤ በግጦሽና በውሃ ሀብት ላይ የሚፈጠር ወቅታዊ ውድድርን ይቀንሳሉ። ሴቶችና ወጣቶችን በመኖ ምርትና ንግድ በማሳተፍም የገቢ ምንጫቸውን ማስፋትና የማህበራዊ መረጋጋትን ማጠናከር ያስችላሉ።
ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር የመኖ ማከማቻ ማዕከላት ከግጦሽ አስተዳደር ጋር በትክክል ሲቀናጁ በግጦሽ መሬት ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳሉ፤ የተፈጥሮ ግጦሽ እንዲያገግም ያግዛሉ፤ ከመጠን ያለፈ ግጦሽንና የአፈር መሸርሸርን ይቀንሳሉ። ይሁን እንጂ ብዙ መኖ ማከማቸት ብቻ የግጦሽ አስተዳደር ችግርን ሙሉ በሙሉ አይፈታም።
በኢትዮጵያ የመኖ ማከማቸት አሰራር በተለያዩ ደረጃዎች እያደገ መጥቷል። በባህላዊ አሰራር በተለይ በደጋና ወይናደጋ አካባቢዎች የሣር ማጨድና ማከማቸት ረጅም ታሪክ ቢኖረውም፣ በአርብቶ አደር ስርዓት ውስጥ ግጦሽን በነፃ የመጠቀም ልማድ ስለሚያመዝን የተከማቸ መኖ አጠቃቀም ብዙም የተለመደ አልነበረም። በተደጋጋሚ የተከሰቱ ድርቆች የመኖ ዋስትና ጉዳይን ወደ መንግስትና የልማት ፕሮጀክቶች ዕቅድ አስገብተውታል። በተለይ ከ2009–2012 ዓ.ም በተለያዩ አካላት ድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች መኖ በማጓጓዝ ድጋፍ ተደርጓል። ከዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አሰራር በመነሳት አቅጣጫው ከ“ድርቅ ከመጣ በኋላ መኖ ማቅረብ” ወደ “ድርቅ ሳይመጣ በፊት ማዘጋጀትና ማከማቸት” እየተቀየረ ነው። በድርቅ ሊያጋጥማቸው በሚችል አካባቢዎች አቅራቢያ የመኖ ማከማቻ መጋዘን እንዲቋቋምና ቀድመው እንዲሞላ ትኩረት እየተሰጠ ይገኛል።
የድርቅ መቋቋም አቅምና ዘላቂ የኑሮ ዘይቤ ማጠናከሪያ ፕሮግራም (DRSLP) ቀጥሎም የአርብቶ አደር ምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት ማሻሻያ ፕሮጀክት (BREFONS) በአፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በ30 ወረዳዎች የተተገበሩ ሲሆን፣ የምርት ስርዓት፣ የውሃ፣ የእንስሳት ጤና፣ የሣር መሬትና ግጦሽ ልማት እንዲሁም የገበያ መሠረተ ልማትን በማጣመር የአርብቶ አደር ቤተሰቦችን ድርቅ የመቋቋምና የማገገም አቅም ለማጠናከር ሠርቷል።
ከእነዚህ ተሞክሮዎች መካከል በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ 72 ሺህ እስር (ቤል) የሚይዝ መጋዘን፤ በቦረና ዞን አሬሮ፣ ዳስ እና ቦርቦር ወረዳዎች እንዲሁም በአፋር አፋምቦ አካባቢ ትላልቅ የመኖ መጋዘኖች መገንባታቸው ይጠቀሳል። በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 3 ወራት ከ22 ሺህ በላይ እስር መኖ ተከማችቷል።
በተጨማሪም በዓለም ባንክ ድጋፍ በሚተገበረው በአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሰት ማሻሻያ ፕሮጀክት በ18 ወረዳዎች የእንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከላት (LCC) ውስጥ የመኖ ማከማቻና ሽያጭ መጋዘኖች ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል። ይህ አቅጣጫ መኖን ከእንስሳት ገበያ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት በተቻለ መጠን መኖ በሚፈለግበት ወቅትና ቦታ በተደራሽነት እንዲቀርብ የሚያግዝ ነው።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶችና ተግባራት የሚገኘው ዋና ትምህርት መጋዘን ብቻ በቂ እንዳልሆነ ነው። ዘላቂ የመኖ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ማከማቻን ከመኖ ምርት፣ ከተገቢ አስተዳደርና ከገበያ ትስስር ጋር ማቀናጀት ያስፈልጋል። የመኖ ባንኮች ዓላማም ድርቅ ከደረሰ በኋላ መኖ ከመፈለግ ይልቅ ቀድሞ በቂ ክምችት መያዝ ነው። በቆላማ አካባቢዎች የመስኖ ልማት፣ የመኖ ምርትና የመኖ ባንክ በአንድነት መፈጸም ወሳኝ ሲሆን የአርብቶ አደሩን ወቅታዊ ፍልሰት፣ የእንስሳት እንቅስቃሴና ባህላዊ አሰራር ግምት ውስጥ ማስገባትም ያስፈልጋል።
የመኖ ማከማቻ ማዕከላት ዘላቂነት የሚወሰነው በማህበረሰብ ባለቤትነትና ተሳትፎ ላይም ይመሰረታል። ህብረት ሥራ ማህበራት፣ የአርብቶ አደር ማህበራትና የማህበረሰብ አስተዳደር ኮሚቴዎች በማዕከላቱ አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ በንቃት መሳተፍ አለባቸው። በተመሳሳይ መኖን በወቅቱ ማጨድ፣ በደንብ ማድረቅና መሰብሰብ፣ ከተቻለ በማሽን ማሰር፣ አየር በሚያስገባ ቦታ ማከማቸት፣ መሬቱ ሲሚንቶ ካልሆነ ከመሬት ከፍ አድርጎ ማስቀመጥና ከዝናብና ከእርጥበት መጠበቅ የመኖን ጥራትና የማከማቻ ጊዜ ለማራዘም ወሳኝ ነው።
