አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለቼክ ሪፐብሊክ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንና ለግብርና ኢንቨስትመንት ያሉ መልካም ዕድሎችን አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ሶፊያ አክለውም የሁለቱ ሀገራት በዘርፉ ተባብሮ መስራት ለምርታማነት እድገት፣ ለቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግርን ለማስፈን ፋይዳው የላቀ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያ በዘርፉ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡

በቼክ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ራዴክ ሩቤሽ በበኩላቸው መንግስታቸው በኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች መገጣጠም ስራ ላይ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለዉ ገልጸዋል።
በዉይይቱ በቀጣይ በሚሰሩ እና ሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ለተግባራዊነቱ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

