አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ከሞዛምቢክ የግብርና፣ አካባቢና ዓሣ ሀብት ሚኒስትር ሮቤርቶ ሚቶ አልቢኖ ጋር ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በማጠናከር በግብርናው ዘርፍ ላይ ልምድ በመለዋወጥ በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡

ውይይታቸውም በዋናነት የሞዛምቢክ መንግስት ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያስመዘገበችውን ስኬት በመቅሰምና በትብብር በመስራት የሁለቱን ሀገራት የወንድማማች አጋርነትን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ሁለቱ ሀገራት የቆየ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ይህንንም የረጅም ጊዜ ግንኙነት በግብርናው ዘርፍ በማስቀጠል ልምድ በመለዋወጥ በትብብር መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
የሞዛምቢክ የግብርና፣ አካባቢና ዓሣ ሀብት ሚኒስትር ሮቤርቶ ሚቶ አልቢኖ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በምርጥ ዘር አቅርቦት፣ በግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ በዲጂታል ግብርና እንዲሁም በሌሎች የግብርና ልማት መስኮች ላይ ልምድ ለመቅሰምና ለመለዋወጥ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ያላቸውን የሁለትዮሽ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በማጠናከር በግብርናው ዘርፍም ልምድ በመለዋወጥ በትብብር ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ማቲዎስ ተገኝ
