አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) የዘንድሮ የአለም የምግብ ቀን “የዛሬ ፈጠራ ለተሻለ ነገ!” በሚል መሪ ሃሳብ በግብርና ሚኒስቴር፣ በተባበሩት መንግሥታት የእርሻና የምግብ ድርጅት እና በዓለም የምግብ ፕሮግራም አዘጋጅነት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ሽግግርን ለማፋጠን በትኩረት እየሠራች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይም የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የመንግሥት፣ የክልሎች፣ የተመራማሪዎች እንዲሁም የልማት አጋሮች ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የኢትዮጵያ ረዳት ተወካይ ወርቅቾ ጃተኖ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግና ድህነትን ለመቀነስ እያደረገ ያለውን ጥረት አብራርተዋል፡፡
ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት እንደሚያጠናክርና እስከ 2030 የሚቆየውን የሀገር ውስጥ ፕሮግራም ማዕቀፍ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዛላታን ሚሊሲች ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እና የሀገር በቀል እውቀቷን በመጠቀም የምግብ ሥርዓቷን ለመቀየር እያከናወነች ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ መስኖን በማስፋፋት፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር እና መስኩን ምቹ በማድረግ ረገድ እየሰራች ያለችውን ስራ ያነሱት ዳይሬክተሩ ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል የልማት አጋር አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዝግጅቱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የልማት አጋር ድርጅቶች፣ ተመራማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ወጣቶችና የግብርና ፈጠራ ባለቤቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
