ኪጋሊ፣ ሩዋንዳ : ነሐሴ 30/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) —ኢትዮጵያ ማሽላን ከተለመደው የሰብል ምርት ባሻገር እንደ ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት፣ የእሴት ጭማሪ፣ የምግብ ሥርዓት ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ አቀረበች።
ይህም በአፍሪካ የምግብ ሥርዓት ፎረም (AFSF) 2026 በኪጋሊ በተካሄደው የማሽላ ኢንቨስትመንት ውይይት ላይ ተገልጿል። ውይይቱ የኢትዮጵያን የማሽላ ዘርፍ አቅም ከካፒታል፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከግሉ ዘርፍና ከገበያ ጋር በማገናኘት የዘርፉን እሴት ሰንሰለት ለማሳደግ ያለውን እድል አጉልቷል።

የAGRA ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ይኼነው ዘውዴ ውይይቱን በመክፈት ተሳታፊዎችን ከእንኯን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላፉበኃላ የውይይቱ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን የግብርና አቅም ከኢንቨስትመንት፣ ከንግድና ከቴክኖሎጂ ጋር በማገናኘት የማሽላ ዘርፍን ወደ ተደራጀና ተወዳዳሪ የእሴት ሰንሰለት ማሸጋገር መሆኑን ገልጸዋል።
በብሔራዊ የማሽላ ፍላግሺፕ ፕሮግራም አማካይነትም ማሽላን ከምርት እስከ ማሰባሰብና ማከማቸት፣ ከማቀነባበር እስከ እሴት ጭማሪ እንዲሁም እስከ ገበያ ድረስ በማስፋት ሊፈጠሩ የሚችሉ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን አመላክተዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ክቡር ዶ/ር ጌታቸው ድሪባ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅምና የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ በስፋት አቅርበዋል።
ዶ/ር ጌታቸው እንዳብራሩት፣ የማሽላ ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን የግብርና አቅም ወደ ምርታማነት፣ ኢንዱስትሪ፣ ንግድና እሴት ጭማሪ ለመቀየር ሰፊ አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥትም የዘርፉን አቅም በመጠቀም የማሽላ እሴት ሰንሰለቱን ከምርት እስከ ማሰባሰብ፣ ማከማቻ፣ ማቀነባበር፣ የእንስሳት መኖ፣ የምግብ ምርትና ገበያ ድረስ ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
የግሉ ዘርፍ በማሽላ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን እንዲያሳድግም መንግሥት ተስማሚ የፖሊሲና የመዋቅር ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ጠቁመዋል። ከእነዚህም መካከል የተሻሻሉ የዘር ሕጎች፣ የኮንትራት እርሻ አዋጅ፣ የግብር ማበረታቻዎች፣ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የተስፋፋ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት መኖራቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር ጌታቸው የኢትዮጵያ የማሽላ ዘርፍ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማርካት ባሻገር ወደ ክልላዊና አህጉራዊ ገበያዎች ለመድረስ ያለውን አቅም አጉልተዋል። በተለይም የCOMESA እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ገበያዎች ተደራሽነት የማሽላ ምርትን ወደ ውጭ ገበያዎች በማስፋት የንግድና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ የማሽላ ፍላግሺፕ ፕሮግራም ልማት ግብረ ኃይል ቴክኒካል መሪ ዶ/ር ማሩ ሸቴ በበኩላቸው የማሽላን የኢንቨስትመንት ጉዳይ በዝርዝር አቅርበዋል። በምርት፣ በምርት ማሰባሰብና ማከማቸት፣ በማቀነባበር፣ በእንስሳት መኖ፣ በምግብ ምርትና በገበያ ልማት ዙሪያ ያሉ የኢንቨስትመንት መስኮችን በማብራራት፣ ማሽላ ሰፊ የእሴት ሰንሰለትና ተጨማሪ የንግድ ዕድሎች ሊፈጥር የሚችል ሰብል መሆኑን አስረድተዋል።
በመዝጊያው ላይ በሩዋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር መስፍን ገብረማርያም የማሽላን አቅም ወደ ተጨባጭ ኢንቨስትመንት፣ እሴት ጭማሪ፣ ንግድና የሥራ ዕድል ለመቀየር የግሉ ዘርፍ አጋርነት እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል። አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ለኢንቨስተሮች ተገማች፣ አስተማማኝና ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢ ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ወደ ፓን አፍሪካ የማሽላ አሊያንስ (Pan Africa Sorghum Alliance) ለመመሥረት የሚደረጉ ዝግጅቶች በተጠናከሩበት ወቅት በኪጋሊ የተካሄደው ውይይት ማሽላን ከተለመደው የሰብል ምርት ባሻገር ለግብርና ለውጥ፣ ለምግብና ሥነ፡ምግብ ዋስትና፣ ለገጠር ኑሮ መሻሻል፣ ለክልላዊ ንግድና ለሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት መስክ አድርጎ ጥምረቱ በይፋ ተመስርቷል።
