በሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ የግብርናዉ ዘርፍ አንዱና ዋነኛው ምሰሶ ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ በትኩረት ከሚሰራባቸው አስር የሰብል አይነቶች አንዱ ስንዴ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጭ የስንዴ ምርትን ወደ ሀገር ዉስጥ ስታስገባ ቆይታለች፡፡ ይህን የተለመደ አካሄድ የቀለበሰ እና የስንዴ ልማቱን በዉጤት ያጀበዉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ኢንሸቲቭ ስንዴን በበጋ እና በክረምት በስፋት በማልማት የሃገር ዉስጥ ፍጆታ በማሟላት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲሁም ስንዴን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬን በማዳን በስንዴ ልማት ላይ በትኩረት በመሰራቱ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በስንዴ ልማት የተገኘዉን እምርታ ቁጥሮች ይመሰሰክራሉ፡፡ በመስኖ የለማ ስንዴ በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 20 ሺህ ሄክታር መሬት በ2017 ምርት ዘመን ወደ 3.5 ሚሊየን ሄክታር አድጎል፡፡ ምርቱንም ከ600 ሺህ ኩንታል ወደ 128 ሚሊዮን ኩንታል ማደግ ችሏል፡፡

በመኸር ወቅት የለማ ስንዴ በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 1.8 ሚሊዮን ሄክታር በ2017 ምርት ዘመን ወደ 4.3 ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ የተቻለ ሲሆን ምርቱንም ከ53 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ተችሏል። በአጠቃላይ በ2017 በጀት ዓመት በስንዴ የለማ መሬት 7.8 ሚሊዮን ሄክታር በመሸፈን 280 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል፡፡

በየዓመቱ በዉጭ ምንዛሬ ይገባ የነበረው ስንዴ በ2017 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ማስቀት የተቻለ ሲሆን ኢትዮጵያ በዓመት በአማካይ ታወጣ የነበረውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት ተችሏል::

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ብሄራዊ የስንዴ ልማት ኢንሸቲቭ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባዉ ስንዴ በራስ አቅም በማምረት ራስን ከመቻል ባለፈ ከአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራች ሀገር አድርጓታል:: በዚህ የስንዴ ራስን የመቻል ስኬታማ ኢኒሼቲቭ ላደረጉት መሪነት ጠቅላይ ሚኒስትራችን በጣሊያን ሮም የተከበረውን የአለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት አግሪኮላ ሜዳሊያ ጥር 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ተሸልመዋል።
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ጌታቸው ምትኩ
