FDRE Ministry of Agriculture

ኢትዮጵያን ከጥገኝነት ያላቀቀው የስንዴ ልማት ስኬት

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ታሪካዊ ስኬት ሀገራችን ከዘመናት የምግብ እርዳታና ከውጭ ስንዴ የማስገባት ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ያላቀቀ ትልቅ ምዕራፍ ነው።

ቀደም ሲል የነበረውን የምግብ እጥረት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰዱ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች እና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥ አስችሏታል።

በሀገራችን የተካሄደው የተቀናጀ አሰራርና ሰፊ የሰብል ማልማት እንቅስቃሴ በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ ትኩረት ማድረጉ የምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።

ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ የሚመረተው ስንዴ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመመደብ ስንዴ ከውጭ ሀገር ይገባ የነበረ ቢሆንም፣ ሀገራችን አሁን ላይ የሀገር ውስጥ ፍላጎቷን በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ችላለች።

በዚህም በ2011 ዓ.ም በ3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ተሞክሮ የነበረው የመስኖ ስንዴ ልማት፣ ዛሬ ላይ ከ3.7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በመሸፈን ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ330 ሚሊዮን ኩንታል በላይ በመሆን የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና አስተማማኝ አድርጎታል።

ሀገራችን በምግብ ራሷን እንድትችል በማድረግ ረገድ ትልቅ መሠረት በመጣል የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ ከመሸፈን አልፎ ምርቱን ወደ ጎረቤት ሀገራት መላክ የሚቻልበት አዲስ የኤክስፖርት ምዕራፍ ተከፍቷል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

በዚህም ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ውጤት እንደ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ባሉ ተቋማት እውቅና አግኝቷል።