አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ ከአዘርባጃን የኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታ ኢልኑር አሊየቭ ጋር በኢትዮጵያ የእርሻና የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፎችን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።

አዘርባጃን ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና በተለይም በሰብል ልማት በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት የገለጸች ሲሆን ይህም ለሁለቱ ሃገራት የኢኮኖሚ ትስስር አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተገልጿል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ የሰብል ልማትን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

ኢትዮጵያና አዘርባጃን በቅርቡ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት የቴክኒክ ቡድን እንደሚቋቋም በውይይቱ ወቅት ተመላክቷል።
ይህ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአዘርባጃን ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው የሁለትዮሽ ትብብር ስምምነት አካል ሲሆን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያለመ ነው።

ዘጋቢ፡- ባህሩ ሰጠኝ
ፎቶ፡- ማቲዎስ ተገኝ
