FDRE Ministry of Agriculture

አየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት

አየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት/Ethiopian Climate Resilient Wheat Value Chain Development (CREW) Project ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በማውጣት የስንዴ ምርትን ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ ስንዴን በበጋና በክረምት በስፋት በማልማት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማዳን የተቻለ ሲሆን የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲሁም ስንዴን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬን ለማዳን በስንዴ ልማት ላይ በትኩረት በመሰራቱ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል፡፡

የተመዘገበውንም ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግስት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ አየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ተግባራ ተገብቷል፡፡

ፕሮጀክቱ ከአፍሪካ ልማት ፈንድ፣ ከኔዘርላንድ መንግስት፣ Global Climate Adaptation (GCA) እና ከመንግስት በተገኘ በጀት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች በ76 ወረዳዎች እየተተገበረ ሲሆን ለአምስት ዓመት ከመንግስትና ከለጋሽ ድርጅቶች 94 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በተገኘ በጀት እየተተገበረ ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማም የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ስንዴ አምራች አርሶአደሮችን ገቢ ማሳደግ ሲሆን ፕሮጀክቱ በይፋ ስራ ከጀመረበት እ.ኤ.አ ግንቦት 20/2024 ጀምሮ የስንዴ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን በክልሎች እያከናወነ ይገኛል፡፡

ለአብነትም የስንዴን ምርታማነትን ለመጨመር የመነሻ ዘር ብዜት በማካሄድ የዘር አቅርቦት ማሻሻል፣ የመነሻ ዘር አቅርቦት ለማሻሻል የፌደራል ስንዴ ምርምር ማዕከላት በሜካናይዜሽንና የዘር መጋዝን የማጠናከር፣በአሲዳማነትና በጨዋማነት የተጠቃ አፈርን ማከም፣ የኮትቻ አፈር አያያዝን ማሻሻል፣ የኖራ ወፍጮና ኤክስካቫተር እንዲሁም የጭነት መኪና በማቅረብ የኖራ አቅርቦት ማሻሻልና የአፈር ለምነት አያያዝ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ፣ የውሃ መስኖ አውታር መሰረት-ልማቶች መጠገንና አዳዲስ መስራት፣ ለርጭት አውሮፕላን የሚያገለግሉ ማኮብኮቢያ ሜዳዎች መገንባት ላይ ፕሮጀክቱ እየሰራ ይገኛል፡፡

ለመስኖ ልማት የሚሆኑ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችና የፓምፖች ጥገና የሜካኒክ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ለማሻሻል የሚያግዙ መሣሪያዎች አቅርቦት ላይም ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በምርምር የወጡት አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ማስተዋወቅ፣ ሰርቶ ማሳያዎችን በመስራት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግ፣ አሲዳማ አፈር ለማከም ኖራ ማቅረብ፣ ሰርቶ ማሳያዎችን በመስራት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የሜካናይዜሽን ማዕከላትን በመገንባት የአርሶአደሩን የሜካናይዜሽን ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ የስንዴ ልማት ኤክስቴንሽን የምክር አግልግሎት በማስፋት የአርሶአደሩን ክህሎትን ማጎልበት፣ የስንዴ ማከማቻዎችን መገንባትና የመሳሰሉ ተግባራት ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ክልሎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ 500 ሺህ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን ስንዴ አምራች አርሶአደር አባወራዎች እና እማወራዎችን ያቀፈ ሲሆን በዚህም 2 ሚሊዮን 300 ሺህ አርሶ አደሮችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡