FDRE Ministry of Agriculture

አየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት የስንዴ ምርታማነትን ለማሻሻል እየሰራ ነው


አዳማ፣ ነሐሴ 21/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የኢትዮጵያ አየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከመንግስት በተገኘ በጀት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች በ76 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓብይ ኮሚቴ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዋና ዋና አፈፃፀም እና በ2019 በጀት ዓመት በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ለመነጋገር ያለመ ውይይት መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ማከናወን የሚጠበቅበትን ተግባራት በተያዘለት የጊዜና የበጀት ዕቅድ መሰረት ለማከናወን ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ አብዱልሰመድ አብዶ የፕሮጀክቱን የ2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና አፈፃፀሞችን አቅርበዋል።

የፕሮጀክቱ ዓላማም የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ስንዴ አምራች አርሶአደሮችን ገቢ ማሳደግ መሆኑንም አስተባባሪው አንስተዋል፡፡

የሴት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለመስኖ ልማት የሚሆኑ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች አቅርቦት ላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ 500 ሺህ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን ስንዴ አምራች አርሶአደር አባወራዎች እና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን አጠቃላይ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ብሔራዊ አስተባባሪው ባቀረቡት ፅሁፍ አብራርተዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው

ፎቶ፦ ጌታቸው ምትኩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *