በሐረሪ ክልል በድሬ ጠያራ ወረዳ የሱቁል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኤሊያስ አብዱረህማን ከአርሶአደርነት ስራቸው ጎን ለጎን በዘመናዊ የወተት ላሞች እርባታ ውጤታማ ናቸው፡፡ “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” ነውና ነገሩ የስኬታቸው መነሻ ፍላጎትና ተነሳሽነት ነበር፡፡

በአንድ ወቅት ከወደ ባቢሌ አካባቢ ነጋዴዎች ሲመጡ አንድ የደረሰች የሀገር ውስጥ ዝርያ ጊደር በ800 ብር ገዙ፡፡ ለዘመናዊ የወተት ላሞች እርባታም መንደርደሪያ ሆነችላቸው፡፡
ጊደሯ ከወለደች በኋላ ለማሳከም የጠሩት ሃኪም ያደረጉላትን እንክብካቤና ንፅህና አይቶ ለከብት እርባታ ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት በመረዳት ስለ ፈረንጅ ከብት እርባታ ሲጠይቀው ለማርባት ፍላጎት እንዳላቸው ገለፁለት::
“ከዚያ ሀረር ከተማ ወስዶኝ 2 የደረሱ ምርጥ ዝሪያ የፈረንጅ ጊደሮችን አሳይቶኝ ሁለቱንም በ4,000 ብር አንድ ላይ እንድገዛ ጠየቀኝ፡፡ ገንዘብ ስላጠረኝ ለጓደኛዬ ነግሬ እሱም አንድ ጊደር እኔም አንድ ጊደር ገዛሁ” አሉን አቶ ኤሊያስ፡፡

ጊደሯ በተገዛች ቀን ፍላጎት አሳይታ በባለሙያ አማካኝነት በሰው ሰራሽ ዘዴ ተዳቅላ ከወለደች በኋላ አንድ የፈረንጅ በሬ በ14 ሺህ ብር ገዝተው የእርባታ ስራቸውን ቀጠሉበት፡፡ አሁን ላይ 17 የተሻሻሉ ዝርያ ላሞችና ጊደሮች ባለቤት ናቸው፡፡
አቶ ኤሊያስ እንደነገሩን በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ በሰው ሰራሽ ዘዴ ማዳቀል ከጀመሩ ወዲህ የሚወለዱት ጊደሮች ብቻ ናቸው፤ የወተት ምርታቸውም እጅግ ተሻሽሏል፡፡
በፊት ከአንድ ላም በአንድ ጊዜ አለባ 5 ሊትር ወተት ሲገኝ አሁን ከአንድ ላም በአንድ ጊዜ አለባ 10 ሊትር ወተት ይገኛል፡፡
አብዛኞቹ ላሞች ያረገዙና ለመውለድ የደረሱ ሲሆን፣ አቶ ኤሊያስ በአሁን ጊዜ ከሚታለቡ ላሞች በየቀኑ 70 ሊትር ወተት ያመርታሉ፡፡
5 ሊትር ለቤት ውስጥ ፍጆታ በማዋል 65 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ አንዱን ሊትር በ120 ብር በመሸጥ በየቀኑ ጥሩ ገቢ ያገኛሉ፡፡
የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በሰው ሰራሽ ማዳቀያ ዘዴ ከመደገፉም ባሻገር በከብቶቹ ጤናና ንፅሕና አጠባበቅ፣ በእንክብካቤ እና ወሊድ ዙሪያ ግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና በመስጠት እየደገፈኝ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ኤሊያስ በዘመናዊ የወተት ላሞች እርባታ ውጤታማ ከመሆናቸውም ባሻገር በአካባቢው እምብዛም ያልተለመደውን ስራ ተግባራዊ በማድረግም ለአካባቢው ማህበረሰብ ሞዴል መሆን ችለዋል፡፡ ወደፊትም እርባታውን ለማስፋፋት እቅድ አላቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው